የምክክር ጉባኤው በተቀመጠለት መርሀ-ግብር መሠረት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው በተቀመጠለት መርሀ-ግብር መሠረት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018(ኢዜአ)፦ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በተቀመጠለት መርሀ-ግብር መሠረት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እየተካሄደ የሚገኘውን የምክክር ጉባኤ አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ምክክሩ አሁን ላይ በስልታዊ ቡድኖች ደረጃ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተመካካሪዎች ከ10 እና ከ50 አነስተኛ ቡድኖች ተነስተው 250 አባላት ባሏቸው ስልታዊ ቡድኖች ውስጥ የደረሱባቸውን ሀሳቦች አጠናቅረው በማቅረብ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በየደረጃው ያሉ ምክክሮች በቃለ-ጉባኤ ተይዘውና ተፈራርመው ወደ ሚቀጥለው ደረጃ እንደሚሸጋገሩ ያመላከቱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ የስልታዊ ቡድኑ ስራ ሲጠናቀቅ ተሳታፊዎቹ ወደ 500 አባላት ዋና ጉባኤ እንደሚሸጋገሩ ገልጸዋል፡፡
ለተመካካሪዎቹም 160 ገደማ አመካካሪዎች እና የተለያዩ የሙያ ዘርፍ ባለሙያዎች እውቀትን መሠረት ያደረገ የተለያዩ ገለጻዎችን እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
በምክክሩ ላይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ምሁራን፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በእኩል ደረጃ እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሁሉም አካላት የሀገርን የጋራ ጥቅም ማዕከል በማድረግ እና የእርስ በእርስ እኩልነትን ባከበረ መልኩ ለምክክሩ ውጤታማነት በጋራ እየመከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቃለ-ጉባኤ ያዦቹ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች መሆናቸውንና እያንዳንዷን ነጥብ ለወደፊት ተመራማሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች በሚጠቅም መልኩ በታማኝነት እየሰነዱ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል፡፡
የምክክሩ ሂደቱ በተቀመጠለት መርሃ ግብር መሰረት በጥሩ ሁኔታ እየካሄደ መሆኑንና ሁሉም ወገኖች ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ እየመከሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡