ቀጥታ፡

ተመካካሪዎች የሀሳብ ልዩነቶችን በመሻገር ለኢትዮጵያ በሚበጁ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018(ኢዜአ)፦በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች ልዩነቶቻቸውን አሻግረው የሀገርን የጋራ ጥቅም በሚያስቀድሙ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

የምክክር ጉባኤው የ250 ስልታዊ ቡድን ውይይት ላይ እንደሚገኝ ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

250 ስልታዊ ቡድኖች በተመደቡባቸው አጀንዳዎች ላይ ባነሷቸውን ሀሳቦች በመነጋገር ቃለ ጉባኤ ይዘው መፈራረም መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የመፈራረሙ ሂደት ዛሬ የሚጠናቀቅ ከሆነ የ500 ጉባኤው ነገ እንደሚጀመር አመልክተዋል።

ስልታዊ ቡድኖቹ በሀሳቦች ላይ የሚያደርጉት ውይይት ከዛሬ የሚያልፍ ከሆነ የ500 ጉባኤው የሚጀመርበት ጊዜ እንደሚራዘምም ተናግረዋል።

በቡድኖቹ ውይይቶች ወቅት የተነሱ ሀሳቦች በአመዛኙ ወደ መግባባት የሚወስዱ መሆናቸውን ጠቅሰው አንዳንዳድ ሀሳቦች በደንብ ማጥራትን እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።

ተመካካሪዎች የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም ትልቁን የኢትዮጵያን ምስል በማየት እየተወያዩ እንደሚገኝና የተሰጣቸውን ሚና በሚገባ እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በተያዘለት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም