የገጠሩን ማህበረሰብ አኗኗር ለማዘመን የተጀመሩ ተግባራት ኑሯችንን ቀይረውልናል - የሞዴል መንደር ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የገጠሩን ማህበረሰብ አኗኗር ለማዘመን የተጀመሩ ተግባራት ኑሯችንን ቀይረውልናል - የሞዴል መንደር ተጠቃሚዎች
ሚዛን አማን፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦መንግስት የገጠሩን ማህበረሰብ የአኗኗር ሥርአት ለማዘመን የጀመራቸው ተግባራት ኑሯቸውን እንደቀየረው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የገጠር ሞዴል መንደር ተጠቃሚዎች ገለጹ።
በሸካ ዞን የኪ ወረዳ የበቆ ሞዴል መንደር ተጠቃሚ አርሶ አደር ደምባሶ ወይሳ ፤ መንግስት የገጠሩን ማህበረሰብ የአኗኗር ሥርአት ለማዘመን የጀመራቸው ሥራዎች የኑሮ ዘይቤያቸውን እንደቀየረው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከቤት እንስሳት ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት የሞዴል መንደሩን ግንባታ ተከትሎ የሰውና የእንስሳት መኖሪያ በተለየበት ሁኔታ በዘመናዊ ቤት መኖር እንደጀመሩ ተናግረዋል። ይህም የግልና የአካባቢ ንጽህናን ለመጠበቅ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ የጌሊት ሞዴል መንደር ነዋሪ አርሶ አደር ከድር ጋንታ፤ ለጥምር እርሻ ምቹ የሆነ ጓሮ በማግኘታቸው በኢኮኖሚ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
መንደሩ በዘመናዊ መንገድ እንዲኖሩ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባለፈ የማር፣ የዶሮ፣ የጓሮ አትክልትና ሌሎች የግብርና ሥራዎችን በማከናወን ኑሯቸው እንዲሻሻል በማድረጉ ውጤታማ እንደሆኑ ተናግረዋል።
መንግስት በገጠር ሞዴል መንደር ግንባታ ኢኒሽዬቲቭ ሠርቶ ያስረከበን ቤት አዲስ ሕይወት በአዲስ ተስፋ እንድንኖር አስችሎናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አልጋነሽ ሙላቱ የተባሉ ተጠቃሚ ናቸው።
በክልሉ የገጠሩን ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸው።
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 16 የገጠር ሞዴል መንደሮች መገንባታቸውን ገልጸው በተያዘው በጀት ዓመትም በ41 የክልሉ ወረዳዎች ለማስፋፋት ይሰራል ብለዋል፡፡
የገጠር ሞዴል መንደር ግንባታ ሥራ የገጠር ትራንስፎርሜሽን አካል ሲሆን ሁለንተናዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ግብን ለማሳካት ከሚያስችሉ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በገጠር ሞዴል መንደር እስካሁን የተገነቡ ቤቶች የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ በጓሮው የሚያመርተው ምግብ ራሱን ከመቻል ባለፈ ለገበያ ጭምር ለማቅረብ ያግዛል ያሉት አቶ ፍቅሬ፣ በሞዴል መንደሩ የገጠርና ከተማ ትስስርን በማሳለጥ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከሰሞኑ ብቻ በቤንች ሸኮ እና ሸካ ዞኖች የተገነቡ አምስት ሞዴል መንደሮች ተገንብተው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል።