ቀጥታ፡

ባለፉት ዓመታት በተካሄደው ዘርፈ ብዙ ሪፎርም አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል-አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 29 /2018 (ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት በተካሄደው ዘርፈ ብዙ ሪፎርም አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንትና የዋና ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለፁ።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት የእቅድ ትውውቅ መድረክ ተካሂዷል፡፡


 

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንትና የዋና ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በፓለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በዲፕሎማሲ ዘርፎች ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች በመከናወናቸው አመርቂ ውጤቶች ተመዝግቧል፡፡

በቀጣይም ሀገራዊ ምክክር የሚፈጥረውን መደላድል በመጠቀም ከሪፎርም ወደ ተሟላ የፖለቲካ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ትግበራን ለማሳካት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

ጽንፈኝነትን በመታገልና የትስስር ትርክት እንዲጎለብት ለማድረግ እንዲሁም ጠንካራ ተቋማትን ለመፍጠር የተጀመሩ የስታንዳርዳይዜሽን ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡


 

በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግስት ጠንካራ መንግስት እና ጠንካራ ሀገር መገንባት የሚያስችሉ ውጤታማ የፓርቲ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን አቶ አደም አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም አመራሩንና አባሉን ጨምሮ ሁሉንም መዋቅር በማነቃነቅ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ተከናውነዋልም ነው ያሉት፡፡

በየደረጃው ያለው አመራርና አባል የተሰጠውን ሃላፊነት በጥራትና በውጤታማነት መፈጸም እንደሚገባው የገለጹት አቶ አደም የጽ/ቤቱ አመራርና ሰራተኛም በበጀት ዓመቱ ለተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም