ሠራዊቱ ሀገርና ሕዝብን ከመጠበቅ ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት መሰረታዊ እሴቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ ሀገርና ሕዝብን ከመጠበቅ ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት መሰረታዊ እሴቱ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገርና ሕዝብን ከመጠበቅ ባሻገር በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት መሰረታዊ እሴቱ እንደሆነ የመከላከያ ሠራዊት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮችና አባላት በመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር በመገኘት የቁሳቁስ ድጋፍና የማዕድ ማጋራት አካሂደዋል፡፡
በመከላከያ ሠራዊት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ እንደገለጹት፤ የመከላከያ ሠራዊቱ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
በዛሬው ዕለትም በመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር በመገኘት ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
ማኅበሩ "ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው" በሚለው መርህ የሚያከናውነው ተግባር የላቀ ሰብአዊነትን የሚያሳይና ለአገር አርአያ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገርና የሕዝብ ሰላም ከመጠበቅ ባሻገር ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን መርዳት የሠራዊቱ መሠረታዊ እሴት መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ ሁለንተናዊ ድጋፍ የአንድ ጊዜ ሳይሆን ሁል ጊዜም ከማኅበሩ ጎን በመቆም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
አረጋውያንንና ሕሙማንን መደገፍ የሁሉም ኃላፊነት መሆን እንደሚገባው ጠቁመው፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ባለሀብቶችና በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎች ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በማኅበሩ ለሚገኙ አረጋውያንና ሕሙማንም "እናንተ የአገራችን ባለውለታና የእኛ አደራ ናችሁ፤ ብቻችሁን አይደላችሁም፣ መላው ሠራዊትና ሕዝብ ከእናንተ ጋር ነው" በማለትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
እርስ በርስ መረዳዳትና መደጋገፍ የኢትዮጵያውያን የቆየ ባህል በመሆኑ፣ ይህንን መልካም እሴት በተግባር በማሳየት አገራዊ አንድነትንና ፍቅርን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለማኅበሩ ላደረገው የቁሳቁስ ድጋፍና ማዕድ ማጋራት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦችም የመከላከያ ሠራዊቱን አርአያ በመከተል ለማኅበሩ የሚችሉትን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።