የምክክር ጉባዔው በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባዔው በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲሉ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ሳዶ ገለጹ።
የሀገራዊ ምክክር ዋና ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የምክክር መድረኩ ከተለምዷዊና ጊዜያዊ የፖለቲካ ድርድሮች በላቀ፣ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከልብ እንዲወያዩና መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በሰለጠነ መንገድ እንዲመካከሩ በርን የከፈተ ነው።
ሂደቱም የዜጎችን እውነተኛ ሐሳብ በማዳመጥና በጋራ እሴቶች ላይ በመመስረት፣ ባለፉት ዘመናት የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የመደማመጥ ባህልን እየገነባ ይገኛል።
በተጨማሪም አስተማማኝና ዘላቂ የሆነ ሀገራዊ ሰላምን በመገንባት የሕግ የበላይነትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦን ያበረክታል።
በጉዳዩ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ሳዶ፤ የምክክር ጉባዔው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገርን ለመገንባትና ዘላቂ ዕድገትን ለማረጋገጥ እንዲሁም አስተማማኝ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት እርስ በእርስ ከሚገፋፋ የፖለቲካ አካሄድ በመውጣት፣ ውይይትና የእርስ በእርስ መተማመን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
መድረኩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በአንድ ቦታ በማገናኘቱ፣ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረና ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
"ሰላም ከራስ አዕምሮና ከቤተሰብ ይጀምራል" ያሉት አቶ ጁነዲን፤ የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት እንጂ የውጭ አካላትን መጠበቅ አስፈላጊ አይደለም ሲሉም አመልክተዋል።
ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ መደማመጥ፣ መቻቻልና መመካከር ለሁሉም ነገር ቁልፍ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ያሉት አቶ ጁነዲን የምክክር መድረኩ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን እንደሚያመጣም እምነታቸው መሆኑን አስታውቀዋል።