በደቡብ ወሎ ዞን የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለውጤት ማብቃት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለውጤት ማብቃት ተችሏል
ደሴ ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ በደቡብ ወሎ ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለውጤት ማብቃት እንደተቻለ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 40 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞችን የመትከል ስራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
በዞኑ ቃሉ ወረዳ የ021 ቀበሌ አርሶ አደር ደጉ መሀመድ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሰጠው ትኩረት ተጠቃሚ አድርጓቸዋል።
ቀደም ሲል ከተከሉት የማንጎ ችግኝ ፍሬ መስጠት በመጀመሩ ዘንድሮ 80 ሺህ ብር መሸጣቸውን ጠቁመው፣ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ በተያዘው ክረምት ወቅትም 130 የማንጎ ችግኝ መትከላቸውን ተናግረዋል።
የዚሁ ወረዳ የ019 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሀመድ ሁሴን በበኩላቸው፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የመሬታችንን የአፈር ለምነት በመጠበቅ የሰብል ምርታማነታችንን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የተከልኳቸውን ችግኞች በአግባቡ በመንከባከብ ለውጤት ማብቃት ችለናል ያሉት አርሶ አደሩ፣ ዘንድሮ የተከልናቸውንም ተንከባክበን ተጠቃሚነታችንን ለማሳደግ እንሰራለን ብለዋል።
ከተከሉዋቸው የባህር ዛፍ ችግኞች ለቤት መስሪያ የደረሰውን በመሸጥ በየዓመቱ እስከ 50 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ የተናገሩት ደግሞ በደሴ ዙሪያ ወረዳ የ038 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይመር አሊ ናቸው።
ከዚህም እያገኙ ያለውን ጥቅም ለማሳደግ ከአንድ ሺህ 500 በላይ የባህር ዛፍ፣ አፕልና ሌሎችንም ችግኞች መትከላቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አርሶ አደሩ በማሳውና በወል መሬቶች ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ያላቸውን ችግኞች በመትከል ተጠቃሚ እያደረገው ነው።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ምርታማነት እንዲጨምር፣ የደን ልማት እንዲጠናከርና የእንስሳት መኖን በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን አብራርተዋል፡፡
በዘንድሮው ክረምትም 40 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ በመትከል የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ዓመት ክረምት 33 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውንም ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።