የሻደይ በዓልን ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የሻደይ በዓልን ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል
ሰቆጣ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ)፡-በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የሻደይ በዓል ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን የባህል ፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል።
መምሪያው የ2018 ዓ/ም የሻደይ በዓል አከባበር ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ይርጋ ማርዬ በመግለጫው ወቅት እንዳሉት የሻደይ በዓል ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የማንነት መገለጫ በዓል ነው ብለዋል።
በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በየዓመቱ ነሃሴ አጋማሽ ጀምሮ የሚከበረውን የሻደይ በዓልን ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን ነው ያስታወቁት።
ስልጣኔ ባልተስፋፋበት ዴሞክራሲ ባልሰፈነበት ዘመን የሻደይ በዓል የሴቶችን ነፃነት በማጎናፀፍ በአደባባይ ወጥተው ባህላቸውን እንዲያከብሩ ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የሻደይ በዓልን "ሻደይን እናከብራለን እሴቶቻችንን እንጠብቃለን" በሚል መሪ ቃል ከነሃሴ 15ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ በደመቀ መልኩ በሰቆጣ ከተማ እንደሚከበር ገልፀዋል።
ሻደይን በአደባባይ ከማክበር ጎን ለጎንም የብሄረሰቡን የባህልና ቋንቋ ጥናት ዙሪያ የፓናል ውይይትን ጨምሮ የንግድ ኢግዚቢሽንና በሌሎች መርሃ ግብሮች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።
የሻደይ በዓል ላይ የዋግን የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ስራ ይከናወናል ያሉት አቶ ይርጋ በክልሉና በፌዴራሉ መንግስት የተገነቡ መሰረተ ልማቶች እንደሚመረቁም ተናግረዋል።
ሻደይ በዓልን ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር አስፈላጊ የሆነ ዝግጅት መደረጉንም ነው የተናገሩት።