ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬት አስተማማኝ የልኬትና የካሊብሬሽን ሥርዓት መገንባት ወሳኝ ጉዳይ ነው - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬት አስተማማኝ የልኬትና የካሊብሬሽን ሥርዓት መገንባት ወሳኝ ጉዳይ ነው - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬት አስተማማኝ የልኬትና የካሊብሬሽን ሥርዓት መገንባት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
19ኛው የአፍሪካ ሥነ-ልክ ድርጅት (ሜትሮሎጂ) ጠቅላላ ጉባዔ "ሥነ-ልክ ለዲጂታል ሽግግር፤ ተዓማኒ ልኬቶች ለአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በጠቅላላ ጉባዔው የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ ደርበው (ዶ/ር) እና የአፍሪካ ሥነ-ልክ ድርጅት (AFRIMETS) ፕሬዚዳንት ሔነሪ ኪበት ሮቲች (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ የዘርፉ ተወካዮች ተገኝተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአንድ የአፍሪካ ሀገር የተመረቱ ምርቶች ተደራራቢ የጥራትና የልኬት ፍተሻዎችን አልፈው ወደ ሌላ ሀገር በነፃነት እንዲዘዋወሩ የተቀናጀ የልኬት ስታንዳርድ መዘርጋት አስፈላጊ ነው።
አህጉራዊ የንግድ ትስስሩ ውጤታማ ሊሆን የሚችለውም ሀገራት ወጥና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የልኬት ቁጥጥር ሥርዓት ሲኖራቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
አክለውም የሜትሮሎጂ ሥርዓትን ማዘመንና ዲጂታላይዝ ማድረግ አፍሪካ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ለላቀ ማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂዎች ዝግጁ እንድትሆን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ከመደበኛ የሥነ-ልክ ሥርዓቶች ጋር በማጣመር የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤቶች አህጉራዊ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማድረግ የንግድ እንቅፋቶችን እንደሚያስወግድም ጠቁመዋል።
የላቦራቶሪ ምርመራዎችንና የካሊብሬሽን አቅምን ማሳደግ የንግድ እንቅፋቶችን ከመቅረፉ ባሻገር፣ አህጉሪቱ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር በታማኝ የልኬት መረጃ ለማስደገፍ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዋ ተቋማዊ አቅምን ለማሳደግ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እና ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ አጋሮች ጋር በመተባበር የሜትሮሎጂ ስታንዳርዶችን ለማጠናከርና የአፍሪካን የኢኮኖሚ ትስስር እውን ለማድረግ ሙሉ ቁርጠኝነቷን አረጋግጣለች።