ቀጥታ፡

ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና መግባባት መሠረትን በማኖር ለትውልዱ የተረጋጋች ሀገርን ለማስረከብ ያስችላል

አዳማ፤ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ):-የምክክር ጉባኤው ለዘላቂ ሰላምና መግባባት መሠረትን በማኖር ለትውልዱ የተረጋጋች ሀገርን ለማስረከብ እንደሚያስችል ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዳማ ከተማ ሀደ ሲንቄና የሀገር ሽማግሌዎችና  ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በዋናነት ለዘመናት የቆዩና ለተለያዩ አለመግባባቶች ምክንያት የሆኑ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በዜጎች መካከል ግልጽ፣ አካታችና ውጤታማ ውይይት እንዲደረግ መድረክ አመቻችቷል፡፡

በውይይቱ የሚነሱ አጀንዳዎችና የሚደረሱ ስምምነቶች የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጠናከር እና ለመጪው ትውልድ የተረጋጋችና በጋራ እሴቶች ላይ የተመሠረተች ሀገርን ለማስረከብ መሠረታዊ ሚናን ይጫወታሉ።

ጉባዔውን በማስመልከት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ሀደ ስንቄና የሀገር ሽማግሌዎች፤ ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና መግባባት መሠረትን በማኖር ለትውልዱ የተረጋጋች ሀገርን ለማስረከብ ያስችላል ብለዋል።

የሀገር ሽማግሌ እና የባህል ፍርድ ቤት ዳኛ ድሪባ ጫላ፣ የምክክሩ ጉባኤ ሀገርን ከምንም በላይ በማስቀደም ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ለማረጋገጥ መሠረት እንደሚያኖር ገልጸዋል።

በምክክሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ተመካካሪዎች ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ የሕዝብ ተወካዮች እንደመሆናቸው መጠን ሙሉ ውክልና እንዳላቸው አመልክተዋል። 

ተመካካሪዎቹ ከብሔር፣ ከዘር፣ ከሃይማኖትና ከፖለቲካ የጸዳ አቋም በመያዝ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ መፍትሔ ያስገኛሉ የሚል ተስፋ መሰነቃቸውንም ተናግረዋል።

ሀደ ስንቄ ዘውዴ ከበደ በበኩላቸው፤ ሀደ ስንቄዎች የሰላም፣ የፍቅር እና የእርቅ ተምሳሌት መሆናቸውን ጠቁመው፣ ሁሉም ዜጋ ከዚህ እሴት በመማር በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሰላምና የሀገር አንድነትን ሊያስቀድም ይገባል ብለዋል።

የምክክሩ ጉባኤ ሀደ ስንቄዎችን ጨምሮ የሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችን በጋራ ማሳተፉ ሀገራችንን ወደ ትክክለኛው ምዕራፍ ለማሸጋገር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል። 

የምክክሩ ጉባኤ ለመጪው ትውልድ ብሩህ ተስፋ ያላትንና የተረጋጋች ሀገርን ለማስረከብ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነም አስረድተዋል።

"እርስ በርስ ከተደጋገፍንና ከተደማመጥን ልንፈታው የማንችለው ሀገራዊ ችግር የለም" ያሉት ደግሞ የሀገር ሽማግሌ ፈይሣ መገርሳ ናቸው። 

አሁን ላይ እየተደረገ ያለው የምክክር ጉባኤ ሀገርን አስቀድሞ በመደማመጥ ለነገው ትውልድ የተረጋጋች ሀገርን ለማስረከብ ብቸኛ መፍትሔን ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ምክክሩ የሁሉም ድምፅና ፍላጎት የሚንፀባረቅበት እንደመሆኑ መጠን መተማመን ላይ በመድረስ ሀገርን ለማጽናት ድልድይ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት አጋርተዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ በምክክር መድረኩ ላይ የሚነሱ ጉዳዮች በሀገሪቱ አስተማማኝ መግባባትን ያመጣሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም