ቀጥታ፡

በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የመክፈቻ ቀን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ)፦ 21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ከዛሬ ጀምሮ በአሜሪካ ኦሬጎን ይካሄዳል።

ዛሬ ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ በሄይዋርድ ፊልድ ስታዲየም በሚጀመረው ሻምፒዮና ላይ ከ147 ሀገራት የተውጣጡ ከ1800 በላይ አትሌቶች ይሳተፋሉ።

ኢትዮጵያም በሻምፒዮናው ላይ በ5000 ሜትር፣ 3000 ሜትር፣ 1500 ሜትር፣ 800 ሜትር (በሁለቱም ፆታዎች)፣ 3000 ሜትር መሰናክል (በሴቶች)፣ 400 ሜትር (በሴቶች) እንዲሁም በርምጃ ውድድር (በሁለቱም ፆታዎች) ትሳተፋለች።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ትናንት ኦሬጎን ደርሷል።

በሻምፒዮናው መክፈቻ ቀን በሁለቱም ጾታዎች የ5000 ሜትር የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

ንጋት 11 ሰዓት ከ53 ላይ በ5000 ሜትር ሴቶች አትሌት ሽቶ ጉሜ እና አትሌት እመቤት ጥላሁን ይወዳደራሉ።

በአጠቃላይ 27 አትሌቶች በፍጻሜው ውድድር ላይ ይሳተፋሉ።

ነገ ጠዋት 12 ሰዓት ከ20 ላይ በሚደረገው የወንዶች የ5000 ሜትር ፍጻሜ አትሌት ዳምጠው ከበደ እና አትሌት ማማሩ ጎዴ የሚሳተፉ ይሆናል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ይከናወናሉ።

ምሽት 4 ሰዓት ከ35 ላይ በሚካሄደው የ800 ሜትር ወንዶች የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ነጋሄ እያሱ እና የሮሳን ግርማ ይሳተፋሉ።

በአምስት ምድቦች ተከፍሎ በሚደረገው የማጣሪያ ውድድር ከየምድቡ ከአንድ እስከ አምስት የሚወጡ አትሌቶች ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያው በቀጥታ ያልፋሉ።

ምርጥ ሰዓት ያስመዘገቡ ሁለት ተጨማሪ አትሌቶች ግማሽ ፍጻሜ ይገባሉ።

ምሽት 5 ሰዓት ከ15 ላይ በሚደረገው የ800 ሜትር ሴቶች የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ደራርቱ ሽብሩ እና ሀብታም ገበየሁ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።

በአምስት ምድቦች በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር፣ ከእያንዳንዱ ምድብ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ የሚወጡ አትሌቶች በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያልፋሉ።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የተሻለ ሰዓት ያስመዘገቡ ሁለት ተጨማሪ አትሌቶች ግማሽ ፍጻሜውን ይቀላቀላሉ።

21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

እ.አ.አ በ2024 በፔሩ ሊማ በተካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 6 የወርቅ፣ 1 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም ሁለተኛ በመሆን ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም