ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ህብረ-ብሔራዊ አብሮነትን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህብረ-ብሔራዊ አብሮነትን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለፁ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ፣ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት እና የቀጣይ ሶስት ዓመት የመካከለኛ ዘመን እና ዓመታዊ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት፤ በጉባኤው የባህል፣ የጥበባት እና ስፖርት ለሀገር ኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ በሳይንሳዊ መንገድ ለመደገፍና በቀጣይ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለመቀየስ የሚያስችል ውይይት እንደሚደረግበት ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ በበጀት ዓመቱ 47 የብሔር ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት እና 5 ሀገር አቀፍ ክብረ በዓላት በተሳካ መንገድ መከበራቸውን ተናግረዋል።

በነዚህ በዓላት ላይ ከ46 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በመሳተፍ ህብረ-ብሔራዊ አብሮነትን ይበልጥ ማጠናከሩን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ባለፉት 28 ዓመታት ስራ ላይ የነበረው የስፖርት ፖሊሲ መሻሻሉን ገልጸው፤ ፖሊሲው ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በ2019 በጀት ዓመት ሙሉ ተቋማዊ ሪፎርም የማድረግና አሰራሮችን የማዘመን ስራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚከናወኑ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ ስፖርት ቱሪዝምን ማስፋፋት የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 


 

ባለሃብቶች ወደ ስፖርቱ ዘርፍ በብዛት እንዲገቡ የማበረታታት ስራ መሰራቱን ጠቅሰው 29 ዓለም አቀፍ የስፖርት ኮንፈረንሶችና ውድድሮች በኢትዮጵያ መካሄዳቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም