ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል እስካሁን ድረስ ከ8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በመኸር አርሻ እስካሁን ድረስ ከ8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።


 

በምርት ዘመኑ በክልሉ ከ11 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ380 ሚሊዮን 659 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ ከ10 ሚሊዮን 199 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን ጠቅሰው፣ ከዚህ ውስጥ ከ8 ሚሊዮን 259 ሺህ በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በኩታ ገጠም ለምቷል ብለዋል።

በሰብል ልማቱ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ አጠቃላይ የክህሎት ማሻሻያና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች መሰጠቱንም አቶ ጌቱ ተናግረዋል። 

በተጨማሪም ለአርሶ አደሩ በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በግብርና ሥራው በዋናነት በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ እና ሌሎች ዋና ዋና የሰብል ዓይነቶች እንዲሁም የተለያዩ የቅባት እህሎች በስፋት እየለሙ መሆኑን አስታውቀዋል። 

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ ግብአት በስፋት መቅረቡን የተናገሩት ኃላፊው፣ በምርት ዘመኑ ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ፣ ከ9 ሚሊዮን 864 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው በክልሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች በኩል እንዲቀርብ መደረጉን ገልጸዋል።


 

እስካሁን በተከናወኑ ተግባራትም ከ6 ሚሊዮን 787 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሮች መከፋፈሉን አክለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የግብርና ምርታማነትን በመጨመር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከቀረበው 673ሺህ 368 ኩንታል ምርጥ ዘር ውስጥ 627ሺህ 953 ኩንታሉ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል።

በአርሶ አደሮች ማሳ ለምቶ የተዘጋጀ ምርጥ ዘርም መቅረቡን ሃላፊው አክለው ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም