በጉጂ ዞን በበልግ ወቅት የለማ ሰብል በኮምባይነር በመታገዝ እየተሰበሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጉጂ ዞን በበልግ ወቅት የለማ ሰብል በኮምባይነር በመታገዝ እየተሰበሰበ ነው
አዶላ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በበልግ ወቅት የለማ ሰብል በኮምባይነር በመታገዝ እየተሰበሰበ መሆኑ ተገለፀ።
በዞኑ የበልግ ወቅት ዝናብ ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ ስለሚጥል የእርሻና የዘር ሥራ የሚካሄድ ሲሆን፤ ምርት ደርሶ የሚሰበሰብበት ደግሞ እስከ ነሐሴ አጋማሽ እንደሚዘልቅ ይታወቃል።
በጽሕፈት ቤቱ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ መንግሥቱ ሂርባዬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፣ በዞኑ በበልግ ወቅት 301 ሺህ 956 ሄክታር መሬት ለምቷል።
ከዚህ ውስጥም ከ240 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በክላስተር መልማቱን ጠቅሰው ከለማው መሬትም ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ዞኑ በገቡ ኮምባይነሮች እና በሰው ኃይል በመታገዝ ምርት የመሰብሰብ ሂደት እየተፋጠነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ ሰብልን በኮምባይነር መሰብሰብ ጊዜንና ጉልበትን ከመቆጠብ ባለፈ፣ የምርት ጥራትን ለማስጠበቅና ብክነትን ለመከላከል የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
እስካሁን በተከናወነው ሥራ ከ149 ሺህ 175 ሄክታር በላይ መሬት ላይ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።
የደረሰው ሰብል አልፎ አልፎ በሚጥል ዝናብ እንዳይበላሽ በርብርብ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ገልፀው በልማቱም ከ129 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን አውስተዋል።
በዞኑ አዶላ ሬዴ ወረዳ የቂልጡ ሶርሳ ቀበሌ አርሶ አደር ሹና ጎበና በሰጡት አስተያየት፣ በበልግ ወቅት በኩታ ገጠም የዘሩት የስንዴ ሰብል ምርታማ እንዳደረጋቸው ገልፀው ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በደቦ ሰብላቸውን እየሰበሰቡ መሆኑን አመልክተዋል።
የተሻሻለ ቴክኖሎጂን መጠቀም እና ሰብልን በመስመርና በክላስተር በመዝራት ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነታቸውን በማደጉ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።