ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ፋይዳው የጎላ ነው

ሰመራ፣ሐምሌ 29/2018(ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክሩ  ለቀጣዩ  ትውልድ የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በአገራችን ለበርካታ ዓመታት የዘለቁ ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ ሂደቶችን በማጠናቀቅ በአዲስ አበባ ውይይት እያካሔደ መሆኑ ይታወቃል።

የውይይቱ ዋና ዓላማ በሀገራዊ ፍላጎቶችና መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር፣ ግጭቶችን ማስወገድ፣ አንድነትን ማጠናከር እና ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች፣ ሰላማዊና ምቹ ሀገርን ማስረከብ ነው።

በሰመራ ሎጊያ ከተማ የሚኖሩ የአቶ አህመድ ሁሴን እና  አቶ ዓሊ መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ምክክሩ  ለዘመናት ምላሽ ባላገኙ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ ወሳኝ ምእራፍ ነው ። 

ምክክሩ ለልጆቻቸው የተሻለች እና የተረጋጋች አገር ለማስረከብ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት አመልክተው በአፋር ባህልም መመካከርና መወያየት ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጠውም ነው የተናገሩት። 

ውይይቱ የኢትዮጵያን ችግሮች በጋራ ለመፍታት አስፈላጊ ከመሆኑም ባለፈ ሰላምን ለማፅናት እና ለሀገረ መንግስት ግንባታ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ነው ያነሱት።

አቶ አህመድ መሐመድ እና አቶ ትኩዬ ይማም በበኩላቸው፤  ምክክሩ የሀገሪቱን  መፃኢ ጊዜያት የተቃና ለማድረግ እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ አቅም እንደሆነም ነው ያመለከቱት። 

በተለይ በሕዝቦች መካከል የነበሩ ዋና ዋና ችግሮችን በመፍታት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው ሲሆን ጠንካራ እና ለሌሎች ተምሳሌት የምትሆን አገር ለመገንባት  ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ይህንን በታሪክ  አጋጣሚ የተገኝ እድል መጠቀም እንደሚገባቸው አመልክተው ምክክሩ በአገሪቱ ሰላም እና ብልጽግና ለማምጣትም የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም