በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የታየው የህዝብ አንድነት ለጋራ ዓላማ በመሰለፍ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የታየው የህዝብ አንድነት ለጋራ ዓላማ በመሰለፍ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው - ምሁራን
ጅማ፤ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ)፡- በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የታየው ህብረትና የህዝብ አንድነት ለጋራ ዓላማ በመሰለፍ ዘላቂና አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጠ ነው ሲሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም ይፋ የተደረገ ሀገራዊ የደን ልማትና የአካባቢ ጥበቃ መርሃ ግብር ነው።
መርሃ-ግብሩ በዋናነት የተወጠነው ፈጣን የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ፣ የመሬት መሸርሸርን ለመግታት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የተመናመነውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ ታስቦ ነው።
በዚህም ባለፉት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን የመርሃ ግብሩ አካል በሆነው በ"በአንድ ጀምበር" የችግኝ ተከላ ንቅናቄ ሕዝቡን በአንድ ላይ በማንቀሳቀስ መትከል ተችሏል።
በዘንድሮው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ንቅናቄም 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘውን ግብ በኢትዮጵያውያን የተቀናጀ ትብብርና ንቁ ተሳትፎ ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል።
ይህን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ በአንድ ጀምበር የተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከተባበርን ሀገራችንን ማሳደግና መለወጥ እንደምንችል በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጥበቡ ዓለሙ (ዶ/ር) ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ችግኝ መትከሉ የኔነት ስሜትን ከመፍጠር ባለፈ ባህል እየሆነ እንደመጣ አመልክተዋል።
የምናከናውናቸው የልማት ሥራዎች ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ የሚያሻግሩና ለቀጣይ ትውልድ መሠረትን የሚጥሉ መሆናቸውን የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላው ስኬት አሳይቶናል ሲሉም አክለው ገልጸዋል።
“የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ባለፉት ዓመታት ተዘርዝረው የማያልቁ ጠቀሜታዎችን አስገኝቷል" ያሉት ዶክተር ጥበቡ፤ ፕሮጀክቱ የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ከመቀየሩም በላይ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
አክለውም ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ ዘርና ቀለም ሳይለይ ዜጎችን በአንድነት ያስተሳሰረ እና ሕብረተሰቡ ችግኝ የመትከልን ጥቅም ይበልጥ እንዲገነዘብ ያደረገ ታላቅ ሀገራዊ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።
መርሃ-ግብሩ የዓለም አቀፍ ተቋማትንና የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት መሳቡን የጠቀሱት ምሁሩ፤ ይህም ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ተፅዕኖ ፈጣሪና አሸናፊ ሀገር መገንባት እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
"የአንድነትን ውጤት ማወቅ የሚፈልግ የዓድዋን ድል እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ማሰብ በቂው ነው" ያሉት ምሁሩ፤ ስንተባበር መገፋፋት እየቀነሰ እና መግባባት እየጎለበተ እንደሚሄድም ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የግብርና እና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የተፈጥሮ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጌትነት ሰይድ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከማሳደግና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ትልቅና ተሻጋሪ ትርጉም ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
"የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አንድነታችን ከሀገር አልፎ ለዓለም ችግር የመፍትሔ አካል እየሆነ ነው" ሲሉም አክለው ገልጸዋል።
በተለይም በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዜጎች ያለ ምንም ልዩነት በየዓመቱ በአንድነት አሻራቸውን ማሳረፋቸው፤ ለሰላማችን፣ ለእድገታችን እና ድህነትን ለማጥፋት ተኪ የሌለው ሚናን ይጫወታል ብለዋል።