ፋይዳቨርስ በዲጂታል ሉዓላዊነታችንና በኢኮኖሚ ዕድገት ጉዟችን አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ፋይዳቨርስ በዲጂታል ሉዓላዊነታችንና በኢኮኖሚ ዕድገት ጉዟችን አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ)፦ ፋይዳቨርስ በዲጂታል ሉዓላዊነታችንና በኢኮኖሚ ዕድገት ጉዟችን አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ዛሬ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረውን ፋይዳቨርስን በይፋ ሥራ አስጀምረናል ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን በመመዝገብ፣ ከ160 ሚሊዮን በላይ የማረጋገጫ አገልግሎቶችን በመስጠትና የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ የዲጂታል ኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት መሆኑን አስመስክሯል ነው ያሉት።
ዛሬ ደግሞ ይህ ስኬታችን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ተሸጋግሮ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር ፋይዳቨርስ በሚል ስያሜ ራሱን የቻለ የመንግስት የልማት ድርጅት በመሆን ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል።
ይህ ውሳኔ ዲጂታል ማንነት ልክ እንደ መንገድ፣ ኃይል እና ቴሌኮሙኒኬሽን ሁሉ ለሀገራችን ተወዳዳሪነትና ዘላቂ እድገት ወሳኝ የሆነ ስትራቴጂካዊ ሀገራዊ መሰረተ ልማት መሆኑን ማረጋገጫችን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከሀገር አልፎ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሰረት ለቀጣናው እና ለአፍሪካ አህጉር ልምድና አቅም በማጋራት የአፍሪካ የዲጂታል ሽግግር መሪ እንድንሆን ያስችለናል። የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዟችን ስኬት የሚለካው በደረስንባቸው ቴክኖሎጂዎች ሳይሆን፣ ሕዝባችን እነዚህን ውጤቶች የራሱ አድርጎ ሲጠቀምባቸው እና ህይወቱ ሲለወጥ ነው።
የቴክኖሎጂ አቅርቦታችንን ጥራት በመጠበቅ፣ የዳታ ደህንነታችንን በማረጋገጥ እና የዜጎቻችንን ዲጂታል ግንዛቤ በማሳደግ የያዝነውን አቅጣጫ በበለጠ ቁርጠኝነት እንቀጥላለን ብለዋል።