ኢትዮጵያ የዲጂታል ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰደች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዲጂታል ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰደች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የዲጂታል ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰደች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተው የ"ፋይዳቨርስ" ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት፤ የ"ፋይዳቨርስ" ሥራ መጀመር ኢትዮጵያ ለዲጂታል ሉዓላዊነቷ የሰጠችውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራሙ ለሀገሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ መገንባቱን ጠቅሰው፤ እስካሁን ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ይህም ከ13 ሚሊዮን በላይ የብሔራዊ መታወቂያ ካርዶች ታትመው መሰራጨታቸው፣ ከ160 ሚሊዮን በላይ የማንነት ማረጋገጫ አገልግሎቶች መሰጠታቸውና በ13 ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች የዲጂታል ማንነት መሠረተ ልማት መዘርጋቱን አስረድተዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራሙ እንደ መንግሥት የልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር "ፋይዳቨርስ" በሚል ስያሜ እንደገና መደራጀቱን ገልጸዋል።
ፕሮግራሙም የኢትዮጵያ ይፋዊ የዲጂታል መሠረተ ልማት ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ እ.አ.አ. በ2030 የኢትዮጵያን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በ6 በመቶ እንዲያሳድግና በቢሊዮኖች ዶላር የሚለካ ቀጥተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲያመጣ ትልቅ ተስፋ እንደተጣለበት ገልጸዋል።
አገልግሎቱ ከነባሩ Fayda ID መተግበሪያ በተሻሻለ መልኩ በFaydaPass አፕሊኬሽን እና በሌሎች ዘመናዊ ዲጂታል ምርቶች የቀረበ በመሆኑ የአገልግሎቱን ተደራሽነትና የመፍትሔ አቅም በእጅጉ እንደሚያሳድግ አስገንዝበዋል።
ዳታ በዘመናችን የኢኮኖሚና የሉዓላዊነት ዋነኛ ምሰሶ በመሆኑ፣ የሀገራዊ መረጃዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ዘመናዊ የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂዎችን እና ጠንካራ የዳታ አስተዳደር ፖሊሲዎችን በተከታታይ መተግበር እንደሚገባ አክለዋል።
ቴክኖሎጂ በገጠርና በከተማ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያገናኝ፣ የአገልግሎት ተደራሽነትን የሚያሰፋና ድህነትን ለመቀነስ የሚያግዝ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።
የዜጎችን የዲጂታል ግንዛቤ ማሳደግ የስትራቴጂው ዋነኛ አካል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ መሠረት የዲጂታል መሠረተ ልማት ልምድን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማጋራት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ይህም ለአህጉራዊ ትብብርና የዲጂታል ዲፕሎማሲ ጠንካራ መሠረት እንደሚሆን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እንደ ሀገሪቱ የሉዓላዊ ሀብት ፈንድ ሀገራዊ ሀብቶችን በብቃት ለማስተዳደር እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
"ፋይዳቨርስ" ወደዚህ ቤተሰብ መቀላቀሉም ዲጂታል ማንነት ልክ እንደ መንገድ፣ ኃይልና ቴሌኮሙኒኬሽን ወሳኝ ስትራቴጂካዊ መሠረተ ልማት መሆኑን የሚያረጋግጥ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ ስኬት እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ የተቋሙ አመራሮች፣ ሠራተኞችና የልማት አጋሮች ምስጋና አቅርበዋል።