ከካይሮ ሴራ ጀርባ፤ የCNN ዘገባ የገለጠው የኢትዮጵያ እውነት - ኢዜአ አማርኛ
ከካይሮ ሴራ ጀርባ፤ የCNN ዘገባ የገለጠው የኢትዮጵያ እውነት
ግብፅ በታሪኳ የዓባይን ወንዝ በብቸኝነት ለመጠቀም የተከተለችው ዋና ስልት "ጠንካራና የተረጋጋች ኢትዮጵያ ለካይሮ ስጋት ናት" የሚል ቀመርን ነው። በመሆኑም በየዘመናቱ የተነሱ የካይሮ መንግስታት ኢትዮጵያ ተረጋግታ ሀብቷን እንዳታለማ ለማድረግ ረዥም ርቀት ተጉዘዋል።
በታሪክ አጋጣሚ የዓባይን መነሻ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር በርካታ የወረራ ሙከራዎችን ያደረገችው ግብጽ፣ በጉንደት (1875) እና በጉራዕ (1876) በተደረጉ ታሪካዊ ውጊያዎች በኢትዮጵያውያን ጠንካራ ክንድ መራራ ሽንፈትን አስተናግዳለች። ከቀጥታ ጦርነት ከተመለሰች በኋላ ካይሮ ስልቷን ወደ "ውስጥ ለውስጥ ማበጣበጥ" ቀይራለች።
ይህም የኢትዮጵያን መንግስት ትኩረትና የፋይናንስ አቅም ከልማት ፕሮጀክቶች (በተለይም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ እና መሰረተ ልማቶች) ወደ ጸጥታ ማስከበር እንዲዞር ለማድረግና ሀገሪቱን ወደማያልቅ የውስጥ ብጥብጥ ለመክተት በርካታ ሴራዎችን ስታከናውን ቆይታለች። ይህ አልሳካ ሲላት ደግሞ የሀሰት መረጃዎችን ማሰራጨትን እንደ አማራጭ መንገድ ስትጠቀም ቆይታለች፤ እየተጠቀመችም ትገኛለች።
የግብፅ የፖለቲካ ምሁራንና ዲፕሎማቶች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ “ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የከፋ ጉዳት ያደርሳል” በሚል የሐሰት ትረካቸውን ሲያሰራጩና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሲያሳስቱ ቆይተዋል። ሆኖም ግን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥበብ የተሞላበት አመራር ሰጪነት ኢትዮጵያ የውጭ ተፅዕኖዎችንና የውስጥ ፈተናዎችን በመሻገር ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት ከፍፃሜ ማድረስ ችላለች። ይህም የመደመር እሳቤ የሆነው ፈተናን ወደ እድል የመቀየር ትልቁ ማሳያ ነው።
የግድቡን እውን መሆን ተከትሎም የካይሮ ተደጋጋሚ የሀሰት ቅሬታና የተዛባ ፕሮፓጋንዳም ዘግይቶም ቢሆን እውነቱ በዓለም ፊት እየተገለጠ ይገኛል።በCNN “Connecting Africa” ወርሃዊ ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ሩባዲሪ ያቀረበችው ዘገባ የዚሁ እውነት ማሳያ ነው። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2020 የቢቢሲ የኮምላ ዱሞር ሽልማት አሸናፊ የሆነችው ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ሩባዲሪ፣ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚገኝበት ጉባ ተገኝታ ባከናወነችው ዘገባ የካይሮን ምናባዊ ቅዥት የሚያፈርሱ ተግባራዊ እውነቶችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ አድርጋለች።
የምህንድስና ልህቀት እና የጋራ ልማት ማሳያ፦
CNN በዘገባው ስለ ሕዳሴ ግድብ ለዓመታት ሲነገር የቆየውን የሀሰት ሴራ ሳይሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የምህንድስናና የግንባታ ባለሙያ ኢትዮጵያዊያን ጥረትን እውን ያደረገ የኢንጂነሪንግ ልህቀት አብነት መሆኑን አጉልቶ አሳይቷል። የግብፅ መንግስት ግድቡን “የስጋት ምንጭ” አድርጎ ለማሳየት ቢጥርም፣ የCNN ዘገባ ግን ግድቡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ቀጣናው የተዘረጋ የጋራ እድገት መድረክ መሆኑን አብራርቷል።
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር መስከረም 2025 በይፋ የተመረቀው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት በማሳደግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት እያበራ መሆኑን በማሳየትም፤ ግድቡ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው ጥረት አካል መሆኑን በተግባር ገልጧል።
የጋዜጠኛ ሩባዲሪ ዘገባ የግብፅን ተደጋጋሚ ቅሬታና ሴራ በሶስት ዋና ዋና ነጥቦች ውድቅ ያደርጋል።
የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ፦
ግድቡ የታችኞቹን የተፋሰሱ ሀገራት የማይጎዳ፣ ይልቁንም የውሃ ፍሰትን በማስተካከልና ደለልን በመቀነስ ረገድ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት፣ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ፕሮጀክት መሆኑን የግድቡ ግንባታ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ሃሳብን በማካተት ጭምር አሳይታለች።
ቀጣናዊ የመደመር እሳቤ ማሳያ ፦
ግድቡ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በመሸጥ ገቢ ከማግኘቷም ባለፈ፣ የቀጣናውን ሀገራት በኃይልና በኢኮኖሚ የሚያስተሳስር ነው። ይህ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሚመራው የመደመር መንግስት እሳቤ ማለትም “በጋራ ማደግ እና እርስ በእርስ መደጋገፍ” የሚለውን ቀጣናዊ ራዕይ በተግባር የሚያረጋግጥ እንጂ ግብፅ እንደምትለው ቀጣናውን ወደ አለመረጋጋት የሚከት አለመሆኑን ያመላክታል።
ሰው ተኮር የኢኮኖሚ ሽግግር፦
በCNN ዘገባ የተካተቱት የኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር (IGC) የኢትዮጵያ ኃላፊ ቴዎድሮስ መኮንን በግልጽ እንዳስቀመጡት፤ 70 በመቶው ህዝቧ ከ30 ዓመት በታች የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከ15 ዓመታት በፊት ከነበረችበት ከአማካይ በታች የነበረ የነፍስ ወከፍ ገቢ አሁን በአፍሪካ ከሚገኙ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት አንዷ መሆን ችላለች። ግድቡም ይህንን ወጣት ኃይል ወደ ዘላቂ ምርታማነት ለመቀየር የሚደረገው ጥረት አካል ነው።
መደምደሚያ፦
በአጠቃላይ ግብፅ ግድቡን መሰረት በማድረግ የምታካሂደው የዲፕሎማሲና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የፖለቲካ ቁማር እንጂ ከሳይንሳዊና መሬት ላይ ካለው እውነት ጋር እንደማይገናኝ የCNN ዘገባ በግልጽ አሳይቷል። በሀገር ውስጥ አቅም እና በጥበብ በተሞላ ሀገራዊ አመራር እውን የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ የኢትዮጵያን መጻኢ የኢኮኖሚ ጊዜ የሚቀርጽ፣ የአፍሪካ ቀጣናን በኃይልና በንግድ የሚያስተሳስር የልማት ማማ እንጂ የትኛውንም ሀገር የሚጎዳ ስጋት አይደለም። የመደመር እሳቤ ያጎናፀፈው ይህ የታሪካዊ ድል ብርሃንም መላውን ቀጣና ማብራቱን ቀጥሏል።