የተጠናቀቀው በጀት ዓመት አዲስ አበባ የዜጎችን ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እመርታዊ ውጤቶችን ያስመዘገበችበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተጠናቀቀው በጀት ዓመት አዲስ አበባ የዜጎችን ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እመርታዊ ውጤቶችን ያስመዘገበችበት ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት አዲስ አበባ የዜጎችን ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እመርታዊ ውጤቶችን ያስመዘገበችበት ዓመት መሆኑ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበራዊ ልማት ክላስተር አፈጻጸምና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊና የማህበራዊ ልማት ክላስተር አስተባባሪ ተወካይ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ እንዳሉት፤ ክላስተሩ በ2018 በጀት ዓመት በቅንጅት የተመሩ በርካታ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል።
በአንድ ተቋም ብቻ ተጀምረው ሊጠናቀቁ የማይችሉና የሌሎች ተቋማትን ትብብር የሚሹ ሥራዎች በጋራ ታቅደው፣ በጋራ ተገምግመው በውጤታማነት መከናወናቸውንም አስታውቀዋል።
በዚሁ መሠረት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራት በቅንጅት በውጤታማነት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ይህ የቅንጅት አሠራር ለሁሉም ተቋማት አቅም የሚፈጥርና መልካም ተሞክሮ በመሆኑ፣ በቀጣይም በሁሉም ዘርፎች ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ፤ በትምህርት ዘመኑ የተመዘገቡ ስኬቶች እንዲሳኩ የማህበራዊ ልማት ክላስተሩ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።
ክላስተሩ ከተማሪዎች ጤና፣ ምገባ፣ ትምህርትና ሥልጠና ጥራትና ቁጥጥር ጋር ተያይዘው የሚከናወኑ ተግባራትን በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በሁሉም የትምህርት ተቋማት የተረጋጋ፣ ሰላማዊና ምቹ የመማርና የማስተማር ሂደት እንዲኖር ማስቻሉን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የተቋማት ክትትል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሞላ ንጉሥ በበኩላቸው፣ በበጀት ዓመቱ በማክበራዊ ዘርፍ እመርታዊ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በ2019 በጀት ዓመትም የተመዘገቡ እመርታዊ ውጤቶችን በማስቀጠል የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የተቋማቱ የቅንጅት አሠራር በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ በመቀጠል የከተማዋን ማህበራዊ አገልግሎቶች የበለጠ ውጤታማና ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።