በሀረሪ ክልል ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራን ለማጎልበት በትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በሀረሪ ክልል ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራን ለማጎልበት በትኩረት ይሰራል
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 28/2018(ኢዜአ) ፦ በሀረሪ ክልል ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራን በማጎልበትና የስራ ፈላጊዎችን የስራ ባህል ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ገለጹ።
የክልሉ የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት የ2018 በጀት አመት የስራ እድል ፈጠራ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2019 በጀት አመት እቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል።
ሰብሳቢዋ በመድረኩ ላይ በክልሉ የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታትና አዳዲስ ቋሚ የስራ እድሎች ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራን በማጎልበት እንዲሁም የስራ ፈላጊዎችን የስራ ባህልና ግንዛቤ ማስፋት ከቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መካከል መሆኑንም ወይዘሮ ሮዛ ተናግረዋል።
በተለይም ገበያ ላይ ተፈላጊ የሆኑ የክህሎት ስልጠናዎችን ከመስጠት ጀምሮ የዜጎችን የስራ ባህል በማሳደግ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በ2019 የበጀት አመት እቅድን ለማሳካት በሚከወኑ ስራዎች የሚገጥሙ ውስንነቶችን ለመቅረፍ በትኩረት መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸው የሚመለከታቸው አካላትም በቅንጅት መስራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
በዚህም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ለስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ከእቅድ ጀምሮ እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ቅድሚያ በመስጠት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ወይዘሮ ሮዛ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ የኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢስማኢል ዩሱፍ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመላከቱት በስራ እድል ፈጠራና ስልጠና ዙሪያ ከልማት አጋር አካላት፣ ከመንግስትና ከግል ሴክተሮች ጋር በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል።
በተጠናቀቀው የበጀት አመትም 11 ሺህ ቋሚ የስራ እድሎችን በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት በገጠርና በከተማ ለሚገኙ ዜጎች መመቻቸቱ ተገልጿል።
በተፈጠረው የስራ እድልም በዋናነት ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ከስደት ተመላሽ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።