ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማኅበረሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው

ቡታጅራ ፤ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለፀ።

በቢሮው "አንድነት ለፅዳት፣ ትጋት ለአገልግሎት፣ ውሳኔ ለልማት" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ የሴክተሩ የምክክር መድረክ በቡታጅራ ከተማ ተካሄዷል።


 

በወቅቱም የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል እንዳሉት በክልሉ የማኅበረሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው።

በዚህም ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸው በኮሪደር ልማትና የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማዘመን ረገድ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የስልጤ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱልሰመድ አብደላ በበኩላቸው በዞኑ ዘመናዊና የተሳለጠ አገልግሎቶችን በመስጠት የተገልጋይ እርካታን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

የኮሪደር ልማት ሥራ ከተሞችን ምቹ፣ ፅዱና ተመራጭ ከማድረግ ባለፈ የገጠር ቀበሌዎች ለኑሮ የተመቹና የወደፊቱን የከተሞች ዕድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲለሙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ለዚህም ስኬት በዞኑ በሚገኙ 3 ወረዳዎች የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘዬ የሚቀይሩ 24 ቤቶች መገንባታቸውንና በዕቅድ የተያዙትን  ቀሪ ቤቶች ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በከተማው በመሬት ዘርፍ በሚሰጡ አገልግሎቶች የሚነሱ የማኅበረሰቡን ቅሬታዎች ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ያሉት ደግሞ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ ናቸው።


 

በተለይም 45 የሚጠጉ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች በመሶብ የአንድ ማዕከል እንዲሰጡ መደረጉ ለውጥ እንዳመጣም ጠቁመዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም