በሀገር አቀፍ ደረጃ ውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል በተከናወኑ የተቀናጁ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ ውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል በተከናወኑ የተቀናጁ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ)፦በሀገር አቀፍ ደረጃ ውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል በተከናወኑ የተቀናጁ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች ውጤት መገኘቱን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ ኮሌራን የማጥፋት ዕቅድና በተከናወኑ ተግባራት ላይ ያተኮረ የሦስት ቀናት የምክክር መድረክ ማካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ እንደገለጹት፤ በክረምት ወቅት የሚከሰቱ የውኃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል ሕብረተሰቡ የታከሙ ውኃዎችን መጠቀምና ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የመከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የተጠቆመ ሲሆን፤ ሕብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገር ሲገጥመው በ 8335 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል መረጃ ማግኘት እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ዝግጁ መሆናቸውንና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ህክምና ማግኘት እንደሚችልም አስረድተው፤ ከዚህ ቀደም የኮሌራ በሽታን ለመከላከል በተከናወኑ የተቀናጁ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
በንጽህና፣ በክትባት እንዲሁም በቅድመ-መከላከል ዘርፍ የተከናወኑት ስኬታማ ተግባራት ኮሌራን ለማጥፋት ያስቻሉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህንኑ ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀረጸው ኮሌራን የማጥፋት ስትራቴጂ ለሌሎች ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስና ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተተገበረ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዚሁ ዘርፍ ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ተግባር ማከናወኗንና በድንበር አካባቢዎችም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ከአጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ይህ የምክክር መድረክም በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ያጠናክረዋል ብለዋል።
በኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር፣ ምላሽና መልሶ ማገገም ዳይሬክተር አቶ መደኃንዬ ሀብተጽዮን በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የሰው ኃይልና የላቦራቶሪ አቅም መገንባቱን ገልጸዋል።
ይህም ፈጣን የልየታ ሥራዎችን ለማከናወንና አፋጣኝ ምላሾችን ለመስጠት ማስቻሉን አብራርተዋል።
በመድረኩ የተገኙት በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የድንገተኛ አደጋዎች ባለሙያ ዶክተር ኢኖሰንት ኮማኬች በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ኮሌራ የሕብረተሰብ ጤና ሥጋት እንዳይሆን ያከናወነችው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ የሚያደርገውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።