በድሬዳዋ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሳደግ የተለያዩ መርሐ ግብሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሳደግ የተለያዩ መርሐ ግብሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው
ድሬደዋ፤ ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሳደግ የተለያዩ መርሐ ግብሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የአስተዳደሩ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው ባለፉት ሁለት ዓመታት የገነባቸውን 367 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዛሬ በዕጣ ለባለዕድለኞቹ አስተላልፏል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኢማጅ አብደላ በከተማው እየጨመረ ለመጣው የቤት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ቢሮው እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለነዋሪዎች በፍትሃዊነት ተደራሽ የማድረጉ ተግባርም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም የ367 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ዕጣ በዲጂታል አሠራር እንዲወጣ ተደርጎ ለቆጣቢዎች መተላለፉን ተናግረዋል።
የአስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር አልይ በበኩላቸው አስተዳደሩ ባለሀብቶችን እና ሕብረተሰቡን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማስተባበር አዳዲስና ነባር ቤቶችን የማደስና የመገንባት ተግባር ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
ለመምህራን የቤት ግንባታ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትም ከባንክ ጋር የማስተሳሰር ስራ መሠራቱን ገልጸው፤ የቤት ልማትን በማጠናከርም በ10/90 እና በ20/80 አሠራር በፍጥነትና ጥራት ለማስተናገድ በትጋት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ከቤት ዕድለኞች መካከል የ08 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሺባን አሜ እና የ04 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገነነ ኃይሉ አስተዳደሩ የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ የሄደበት ርቀት የሕዝብን ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ተናግረዋል።