በዞኑ የፍትህ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የማስደገፍና የማዘመን ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የፍትህ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የማስደገፍና የማዘመን ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዳማ ፤ሐምሌ 28/2018(ኢዜአ)፡-በምስራቅ ሸዋ ዞን የህግ የበላይነትን ለማስከበር የፍትህ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የማስደገፍና የማዘመን ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ አስገነዘቡ።
የምስራቅ ሸዋ ዞን ፍርድ ቤቶችና የፍትህ አካላት የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ 7ኛው የምክክር ጉባኤ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በዞኑ የፍትህ አገልግሎትን ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ዘመናዊ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸዉን ገልፀዋል።
በተለይም በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበረው የህዝብ ቅሬታ እየተቀረፈ መምጣቱን ያመለከቱት አቶ አባቡ፤ የተካሄደው የፍትህ ማሻሻያ ሪፎርም የህብረተሰቡን የመንግስት አገልግሎት እምነት ያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘርፉ አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም የተገልጋዮችን እንግልትና ምልልስ ማስቀረት፣ የሐሰት ምስክርነትን ማጥፋት እንዲሁም የመልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም በዞኑ ጥራት ያለው፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዲጂታላይዜሽን ስራ በወረዳ ፍርድ ቤቶች በተጠናከረ መልኩ ስራ ላይ ሊውል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዘውዴ ፍቃዱ በበኩላቸው፤ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና ጥራቱን ለማስጠበቅ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፈጣንና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና የተገልጋይን እርካታ ለማረጋገጥ በወረዳና በዞን ፍርድ ቤቶች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በስፋት ስራ ላይ መዋሉንም ጨምረው ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ቀርበው ከነበሩት ከ23 ሺህ በላይ የክስ መዝገቦች ውስጥ ከ22 ሺህ 900 በላይ የሚሆኑት እልባት ማግኘታቸውን እንደ አብነት ገልጸዋል።
በቀጣይነት የፍትህ ዘርፉን ጥራት ለማረጋገጥ በተለይም በበየነ-መረብ አማካኝነት ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው ክርክር፣ ምላሽና ውሳኔ እንዲያገኙ መደረጉን ያመለከቱት ፕሬዝዳንቱ፤ በ2019 ዓ.ም የዞኑን የፍትህ አገልግሎት ከወረቀት ንክኪ ነፃ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት አገልግሎቱን ከወረቀት ንክኪ ነፃ ለማድረግ እንዲቻል 98 ሺህ መዝገቦች ወደ ሶፍት ኮፒ የተቀየሩ ሲሆን፤ ለዲጂታል አገልግሎትም ዝግጁ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
በጉባዔው ላይ በየደረጃው ካሉ የዞኑ ፍርድ ቤቶች፣ ዐቃቤ ህጎች፣ የፀጥታ አካላትና አመራሮች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ተሳታፊ ሆነዋል።