ቀጥታ፡

በምክክር ጉባኤው ልዩነቶችን በምክክር በመፍታት ሀገራዊ መግባባት የሚፈጥሩ ምክረ-ሃሳቦች ይጠበቃሉ - ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ልዩነቶችን በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ መግባባት የሚፈጥሩ ምክረ-ሃሳቦች እንደሚጠበቁ ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ዋናው የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት በዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ነው፡፡

ከተመካካሪዎች መካከል አቶ ኦንጎላይ ጎሻንዶ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምክክር ጉባኤው በኢትዮጵያ ትክክለኛና የማያሻማ ዘላቂ ሰላም መፍጠር የሚያስችል ትልቅ ተስፋ ያነገበ ነው፡፡

የተለያዩ አመለካከቶችና ሀሳቦችን በነጻነት በማንፀባረቅ ለመጪው ትውልድ የተሻለችና የተረጋጋች ሀገር ለመገንባት ጉባኤው መሰረት ይጥላል ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ሳሮን አመነው በበኩሏ፤ መድረኩ የመላ ኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ በግልጽ የተንጸባረቀበት መሆኑን ገልጻለች።

ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን በነፃነት በመግለጽ ልዩነቶችን እያጠበቡ ወደ ጋራ መግባባት መምጣት የሚችሉበት መሆኑን ተናገራለች፡፡

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የህዝብና አደረጃጀቶች ተወካይ ተመካካሪዎች በአንድ መድረክ መገናኘታቸው ሀገራዊ አንድነትን ይበልጥ ይገነባል የያሉት ደግሞ አቶ ስርዓት ደንግሬቲ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን በተወካዮቻቸው አማካኝነት በጋራ መምከራቸው የጋራ ሀገራቸውን በአንድነት ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም