ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቷን ቀጣዩ የኢኮኖሚዋ ምሰሶ እያደረገች ነው- ሲኤንኤን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቷን ቀጣዩ የኢኮኖሚዋ ምሰሶ እያደረገች ነው- ሲኤንኤን
የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ሩቢዳሪ በኢትዮጵያ ላይ በሚያተኩረው ዘገባዋ በሀገሪቱ ኮረብቶች ያለውን ወርቅ ጨምሮ ከፍተኛ የብረት ማዕድናት አምራች ለመሆን እያደረገች ያለውን ጥረት መመልከቷን ተናግራለች።
በዘገባዋ ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ የሃይል ሚዛን መሆን እንደምትፈልግ ገልጻ፤በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው ኩርሙክ የወርቅ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የማዕድን ኢንቨስትመንቶች ውስጥ በዋናነት የሚጠቅስ መሆኑን ተናግራለች።
በምዕራብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ከለበሱት ከፍተኛ የኮረብታ ስፍራዎች ላይ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን የሚያስገኙ ከፍተኛ የወርቅ ሀብቶች እንዳሉ እና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ብቅ እያሉ መሆኑን ትናገራለች።
በሺዎች የሚቆጠሩ የግንባታ ባለሙያዎች እና ማዕድን አውጪዎች በኢትዮጵያ ግዙፍ የሆነውን የወርቅ ማዕድን ፋብሪካ ግንባታ እያከናወኑ እንደሚገኝ ገልጻለች።
በስፍራው የሚገኙ የማዕድን እና ጂኦሎጂ ባለሙያዎች የወርቅ ማዕድኑን የማጣራት ስራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጻለች።
ጋዜጠኛዋ የወርቅ ማጣራት እና ምርት ሂደቱን በተመለከተ ከባለሙያዎች ማብራሪያ ማግኘቷንም አመልክታለች።
ወርቁን የማግኘት ሂደቱ እጅጉን ፈታኝ እና አድካሚ እንደሆነ ገልጻ፥ይሁንና ልፋቱ ትልቅ ጠቀሜታ የሚያስገኝ መሆኑን ተናግራለች።
የወርቁን ግብአት ውጪ ሀገር ልኮ ከማጣራት ይልቅ በኩርሙክ የወርቅ ማዕድን ፋብሪካ የራሱ ማጣሪያ ፕላንት እንዳለው በጉብኝቷ ወቅት መረዳቷን አመልክታለች።
የሲኤንኤኗ ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ሩቢዳሪ ወርቅ የሀገሪቷ ዋና የወጪ ንግድ ገቢ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ገልጻለች።
ባለፈው ዓመት በወርቅ የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ከፍተኛ መሆኑን ተናግራለች።
ይህም የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ውጥኖች በግልጽ የሚያሳይና ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቷን ቀጣዩ የኢኮኖሚዋ ምሰሶ እያደረገች እንደምትገኝ ሲኤንኤን በዘገባው አስረድቷል።