ቀጥታ፡

ታዋቂው ሲ ኤን ኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

ታዋቂው የሲኤንኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባለፈ የቀጣናው ሀገራትን የኢነርጂ ተጠቃሚ ያደረገ  ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን በዘገባው አስቃኝቷል።
 
ግድቡ በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ብርሃን ያደረሰ መሆኑንም አመላክቷል።

በሲኤንኤን ዘጋቢ የሆነችው ቪክቶሪያ ሩባዲሪ ባሰናዳችው ዘገባ÷ ወደ ጉባ በማቅናት የግድቡን እውነታ አስቃኝታለች።
 
በዚህም  በሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ የምህንድስና ባለሙያዎች እና የግንባታ ባለሙያዎች ሸለቋማ የሆነውን አካባቢ ወደ አፍሪካ ግዙፍ ግድብ መቀየራቸውን ገልጻለች። ግድቡ የምህንድስና ልህቀት የታየበት ነውም ብላለች።
 
ከ14 ዓመታት የግንባታ ቆይታ በኋላ ህዳሴ ግድብ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር መስከረም  2025 መመረቁን ገልጻለች።



 
ግድቡ በኢትዮጵያውያን ድጋፍ፣ የመንግስት ፋይናንስ፣ ቦንዶች እና የተለያዩ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ አማራጮች በኢትዮጵያዊያን አቅም መገንባቱን ተናግራለች።
 
ይህ ግዙፍ ግድብ ለሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያውን ብርሃን የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን  በጎረቤት ሀገራትም የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እንዲደርስ የሚያደርግ ነው።

በዚህም  ግድቡ ከኢትዮጵያ ባለፈ የቀጣናዊ ኃይል ትስስር ማእከል እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻ በመሆን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግራለች።

ሲኤን ኤን በዘገባው ላይ  የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮን በማቅረብ ኢትዮጵያ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መልኩ ግድቡን እየተጠቀመች መሆኑን አመላክቷል።



 
ግብፅ በግድቡ ምክንያት የሚደርሳት ውሃ ቀንሷል በሚል የምታቀርበው ክስ መሰረተ ቢስ መሆኑንም ኢንጂነር ክፍሌ  አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ በሕዳሴ ግድቡ የሚገኙ 13 ተርባይኖች በሚያመነጩት ሀይል 6 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ ሀይል ተደራሽ ማድረግ መቻሉን፣ በቀጣይ ደግሞ ለሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ሀይል ለመሸጥ ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም በሕዳሴ ግድቡ በተፈጠረው ንጋት ኃይቅ ላይ የተፈጠሩት ደሴቶች ለቱሪስት መስህብነት ትልቅ አቅም መሆናቸውን በማንሳት ፤ በቀጣይም ለቱሪስት መዳረሻነት የሚያገለግሉ መሰረተ ልማቶች እንደሚገነቡ  ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም