ቀጥታ፡

በክልሉ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል

ቡታጅራ ፤ ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ) ፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው አንድነት ለፅዳት፣ ትጋት ለአገልግሎት፣ ውሳኔ ለልማት በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው  የምክክር ጉባኤ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በወቅቱ እንዳሉት፤ በ2018 በጀት ዓመት በክልሉ ከተሞችን  በማህበረሰብ ተሳትፎ  በማልማት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ተችሏል።

በክልሉ መንግስት ለከተሞች ልማት  ከመደበው በጀት ባለፈ  ህብረተሰቡ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ማዋጣቱን ተናግረዋል።

በዚህም  የውስጥ ለውስጥ አስፓልትን ጨምሮ የመንገድ፣ የውሃና ሌሎች መሰረተ ልማት ስራዎች ተደራሽነትን በማስፋት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

ከተሞችን ውብና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በክልሉ ሰባት ከተሞች በሁለት ምዕራፍ 165 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉን ከተሞች የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከርና የተስተዋሉ ጉድለቶችን ለማረም የምክክር መድረኩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል። 

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደሱ አበጋዝ በበኩላቸው፤ በዞኑ በበጀት ዓመቱ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የልማት ስራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ስለመደረጋቸው ተናግረዋል።


 

ከተሞችን ውብና ፅዱ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በተጀመሩ ስራዎች በቡታጅራ ከተማ በመጀመሪያ ምዕራፍ እየተተገበረ ከሚገኘው 21 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ውስጥ 11 ነጥብ 26 ኪሎ ሜትር የሚሆነው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ስለመደረጉም ጠቅሰዋል።

የከተማዋን  የአገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን የማህበረሰቡን  እርካታ  ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም  ገልጸዋል። 

በምክከር መድረኩ የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም