ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይልን ለኤሌክትሪክ ማመንጨት ለመጠቀም በያዘችው ዕቅድ መሠረት ዓለም አቀፍ የቁጥጥርና የሕግ ማዕቀፏን እያጠናከረች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይልን ለኤሌክትሪክ ማመንጨት ለመጠቀም በያዘችው ዕቅድ መሠረት ዓለም አቀፍ የቁጥጥርና የሕግ ማዕቀፏን እያጠናከረች ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይልን ለኤሌክትሪክ ማመንጨት ለመጠቀም በያዘችው ዕቅድ መሠረት ዓለም አቀፍ የቁጥጥርና የሕግ ማዕቀፏን እያጠናከረች መሆኗን የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን በኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ባዘጋጀው ረቂቅ የቁጥጥር ደንብ ዙሪያ ከመንግሥት ተቋማት፣ ከሙያ ማኅበራትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሰሎሞን ጌታቸው (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂን ለሰላማዊ ዓላማና ለኤሌክትሪክ ማመንጨት የመጠቀም ፍላጎቷን ለዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በይፋ ካሳወቀች በኋላ፣ የቁጥጥር ሥርዓቱን ለማጠናከር ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ሂደት የሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የሕግና የቁጥጥር ማዕቀፎች ዝግጅት፣ የፈቃድ አሰጣጥ እንዲሁም የኢንስፔክሽንና የሕግ ማስከበር ሥርዓቶች በዓለም አቀፍ መስፈርቶች መሠረት እየተገነቡ ይገኛሉ ብለዋል።
የኒውክሌር ጣቢያዎች ቦታ መረጣ፣ የአካባቢና የሕዝብ ደኅንነት ጥበቃ፣ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች መከላከል እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ መስፈርቶች በረቂቅ ደንቡ ውስጥ መካተታቸውን ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ ከአሜሪካ የኒውክሌር ቁጥጥር ኮሚሽን (USNRC)፣ ከሩሲያው የቁጥጥር ተቋም (Rostechnadzor) እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር የአቅም ግንባታና የሙያ ትብብር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በውይይቱ ከባለድርሻ አካላት የሚሰበሰቡ ግብዓቶች ረቂቅ የቁጥጥር ደንቡን በማሻሻልና ለማጽደቅ መሠረት እንደሚሆኑም ገልጸዋል።