የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት የምግብ ሉአላዊነት እንዲረጋገጥ እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት የምግብ ሉአላዊነት እንዲረጋገጥ እያስቻለ ነው
ወልቂጤ፤ ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት የምግብ ሉአላዊነት እንዲረጋገጥ እያስቻለ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ እንዲሁም በቀቤና ልዩ ወረዳ ኩታ ገጠም የበቆሎ እርሻዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የግብርና ሜካናይዜሽንና የኩታ ገጠም እርሻ የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል ።
ለዚህም ለአርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና የግብአት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ በቅንጅት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
የግብርና ምርትና ምርታማነት እያደገ በመምጣቱም የምግብ ሉአላዊነት እየተረጋገጠ እንዲመጣ እያስቻለ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህም የአርሶ አደሩን ገቢ በማሳደግ የኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማፋጠን የራሱን አቅም እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው፤ በጉራጌ ዞን በአበሽጌ ወረዳ እንዲሁም በቀቤና ልዩ ወረዳ በበቆሎ ልማት የመጣው ለውጥ የአርሶ አደሩ የግብርና ሙያተኞችን ምክር የመከተል ውጤት ነው ብለዋል።
ቢሮው ምርታማነትን ለማሳደግ የኩታ ገጠም አሰራር ተግባራዊ እንዲሆን ከመድረግ ባለፈ የምርት ብክነትን የሚቀንሱ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
የዚሁ ማሳያ የሆነው የኩታ ገጠም የበቆሎ ልማትም ሰብሉን ለመንከባከብና ዘመናዊ አመራረትን ለመተግበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በዘርፉ የመጣውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራም አመላክተዋል።