በአማራ ክልል የፍራፍሬ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የፍራፍሬ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው
ደሴ ፤ ሐምሌ 28/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው የፍራፍሬ ልማት የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ ገለፁ።
የአማራ ክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች በቃሉ ወረዳ በክላስተር የለማ ፍራፍሬ ልማት ጎብኝተዋል።
የቢሮ ኃላፊው አቶ ደረጀ ማንደፍሮ እንደገለፁት፣ ክልሉ ለፍራፍሬ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል።
ባለፉት ሰባት ዓመታትም ቡናና አቮካዶን ጨምሮ ሌሎች የፍራፍሬ አይነቶች በመመረታቸው ከፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ጭምር ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።
በክልሉ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩን በማደራጀት በኩታ ገጠም የፍራፍሬ ልማት እንዲሳተፍና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም 37 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ26 ሚሊዮን በላይ የቡናና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በቃሉ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማው የፍራፍሬ ችግኝም ተስፋ ሰጭና ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በበኩላቸው፣ ዞኑ ለፍራፍሬ ልማት ያለውን ምቹነት በመጠቀም የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግና ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
አርሶ አደሩን በማደራጀት በኩታ ገጠም ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካን፣ አቮካዶና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በማልማት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራም ሶስት ሺህ 700 ሄክታር መሬት በፍራፍሬ ችግኝ እየተሸፈነ እንደሚገኝ ጠቁመው አሁን ላይ መስኖን በመጠቀም በበጋ ጭምር የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል መቻሉን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ የፍራፍሬን ጥቅም በተግባር በማየቱ በኩታ ገጠም እየተደራጀ ማልማት ጀምሯል ያሉት ደግሞ የቃሉ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን አህመድ ናቸው።
በዚህም በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡና በሽታን የሚቋቋሙ ዝርያዎችም በመንግስት እየቀረቡላቸው ነው ብለዋል።
በቃሉ ወረዳ የ033 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙባረክ መሀመድ እንደገለጹት ፣ ፍራፍሬን በክላስተር ማልማት መቻላቸው ተጠቃሚ አድርጓቸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተከሉዋቸው የማንጎና ሙዝ ችግኞች ለገበያ በማቅረብ በዘንድሮ ዓመት ብቻ ከ70 ሺህ ብር በላይ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በዘንድሮው ክረምትም ተጨማሪ 200 የማንጎ ችግኞችን መትከላቸውን ተናግረዋል።
በጉብኝቱ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችና አባላትን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።