ቀጥታ፡

በአንድ ጀምበር የተጻፈ ታሪክ፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት

የአንድ ሀገር የታላቅነት መለኪያዎች አንዱ የታቀዱ አገራዊ ግቦችን ወደ ተጨባጭ ተግባር የመለወጥ ብቃት ነው።

ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ፣ 805.3 ሚሊዮን በመትከል ያስመዘገበችው አዲስ ታሪካዊ ስኬት፣ አገሪቱ ያቀደችውን በተግባር ማሳየት የምትችልና ትልልቅ ህልሞችን የመተርጎም አቅም ያላት ታላቅ አገር መሆኗን ለመላው ዓለም አስመስክሯል።

በአንድ ቀን ውስጥ የተከናወነው ይህ ግዙፍ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በርካታ ጥልቅ ትርጉሞችን አዝሏል።

በአንድ ጀምበር ከ805.3 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ከፍተኛ የሎጂስቲክስ፣ የቅድመ-ዝግጅትና የህዝብ ንቅናቄ ሥራን ይጠይቃል።

ይህ ስኬት አገሪቱ ማንኛውንም ታላቅ አገራዊ እቅድ እስከ መጨረሻው የትግበራ ምዕራፍ ድረስ በብቃት የመምራትና የማስተባበር ተቋማዊና ህዝባዊ አቅም እንዳላት ማረጋገጫ ነው።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በዕድሜ፣ በጾታ ወይም በሌሎች ልዩነቶች ሳይወሰኑ በአንድ ቀን ለአንድ ተመሳሳይ አገራዊ ዓላማ መቆማቸው፣ ኢትዮጵያውያን ለጋራ እድገታቸውና ለወደፊት ተስፋቸው ያላቸውን ጽኑ ፍላጎትና አንድነት ያሳያል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥና የበረሃማነት መስፋፋት ዋና ስጋት በሆኑበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባራዊ እርምጃ ለችግሩ መፍትሔ በመስጠት ረገድ ዓለም አቀፍ መሪነቷን ያስመሰከረችበት አጋጣሚ ነው።

ይህ ስኬት አገሪቱ የገጠሟትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች ተሻግራ፣ አቅሟን አስተባብራ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምትችል ለዜጎቿም ሆነ ለውጭው ዓለም የሰጠችው ትልቅ የራስ መተማመንና የተስፋ መልዕክት ነው።

በአጠቃላይ፣በአንድ ጀምበር የተከናወነው ይህ ታሪካዊ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ አርቆ የማሰብና የማቀድ ችሎታዋን ብቻ ሳይሆን፣ያቀደችውንም በአንድነትና በቁርጠኝነት ወደ መሬት በማውረድ በተግባር የምታሳይ ታላቅ አገር መሆኗን በግልጽ ያረጋገጠ አኩሪ ተግባር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም