ካቀደችው በላይ በማሳካት የአካባቢ ጥበቃ ተምሳሌትነቷን በድጋሚ ለአለም ያስመሰከረች ታላቅ ሀገር - ኢዜአ አማርኛ
ካቀደችው በላይ በማሳካት የአካባቢ ጥበቃ ተምሳሌትነቷን በድጋሚ ለአለም ያስመሰከረች ታላቅ ሀገር
ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ ብዙ አስደናቂ ክንውኖችን አሳልፋለች፤በህዝቦቿ አይበገሬነት፣ አንድነትና ትጋት አለምን ያስገረሙ በርካታ ድሎችን ከአድዋ ድል ጀምሮ ተቀዳጅታለች።
አሁን ደግሞ በ2018 ዓ.ም የክረምት ወቅት ሌላ ደማቅ ገድል ፈጽማለች።
ኢትዮጵያ ትናንት በአረንጓዴ ዐሻራ 800 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር ለመትከል አቅዳ 805 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ከእቅድ በላይ ማሳካቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በዚህም ሀገራችን ከራሷ አልፋ ለመላው አፍሪካ ታላቅ ምሳሌ መሆን መቻሏን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብስረዋል፡፡
በዚህ ደማቅ ሀገራዊ የችግኝ ተከላ ንቅናቄ ላይ 26 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች በነቂስ ወጥተው እጅግ ከፍተኛ እና የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውን በመግለጫቸው አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ላሳዩት አስደናቂ ርብርብ እና ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚሁ የአንድ ጀምበር ተሳትፎ 291 ነጥብ 4 ሺህ ሄክታር መሬት የአረንጓዴ ዐሻራ መልበስ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ይኸውም በአንድ ጀምበር 805 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የራሷን ክብረ ወሰን በድጋሚ በማሻሻልና ለተቀረው አለም አዲስ ትምህርት መስጠት ችላለች።
ይህ ታላቅ ሀገራዊ መርሃ ግብር አረንጓዴ ዐሻራ ከ2011 ዓ.ም አንስቶ ላለፉት ሰባት ዓመታት በስኬት ሲተገበር የቆየውና ዓለም አቀፍ እውቅናን ያተረፈው የልማት ስራ አካል ነው።
በአንድ ቀን 805 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ማለት ዛፍ ከመሬት ጋር ከማዋሃድ ባለፈ ጥልቅ የሆነ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ትርጉም አለው።
ይህ ድርጊት የኢትዮጵያን ህዝብ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት፣ ዓለም አቀፋዊውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያደርገውን የማያቋርጥ ጥረት እና ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴና ምቹ የሆነች ሀገር ለማስረከብ ያለውን የላቀ ራዕይ በግልጽ ያሳየችበት ሆኗል።
ይህ ግዙፍ ሀገራዊ ግብ ለማሳካት የእያንዳንዱ ዜጋ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነበር። ህፃናት፣ ወጣቶች፣አዛውንቶች፣ የመንግስትና የግል ሰራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮችና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዚህ ታሪካዊ ቀን ከዳር እስከ ዳር በመውጣት አሻራቸውን አሳርፈዋል።
ዛሬ የተከልነው እያንዳንዱ ችግኝ የነገው ተስፋችን፣የልጆቻችን ንጹህ አየር እና የሀገራችን የብልጽግና መሰረት ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አካባቢን ከማለምለም ባለፈ፣ የዜጎችን የተቀናጀ አቅምና ሀገራዊ ራእይ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።