ቀጥታ፡

የተከልነው ችግኝ የነገ ተስፋችንን የሚያለመልም ነው- በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 27/2018(ኢዜአ)፡- የተከልነው ችግኝ የነገ ተስፋችንን የሚያለመልም ነው ሲሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ተናገሩ።

በሀዋሳ ከተማ 15ኛ ዙር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጠናን እየተከታተሉ ያሉ ወጣቶች በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተሳትፈው አሻራቸውን አሳርፈዋል።

ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ወጣት መስከረም አበራ፤ሙሉጌታ ሀይሌ እና ወጣት ተመስገን አሼቦ እንዳሉት ዛሬ የተከልናቸው ችግኞች የነገ ተስፋዎቻችን በመሆናቸው ከተከላው ባሻገር የእንክብካቤው ስራ ላይ እንሳተፋለን።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያስገኝ ካለው ጠቀሜታ ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ የለማች ሀገር ለማስተላለፍ  ወሳኝ ምእራፍ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የህዝቦች አንድነትና ትስስር እያጠናከረ መምጣቱን አመልክተው ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡት የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሳትፎም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ ከተጀመረ ወዲህ በግብርና፣ ኢንዱስትሪና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል  በሚሰማሩበት አካባቢ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ነው ያረጋገጡት።

የስልጠውና አስተባባሪ ወይዘሮ አበባ ተገኝ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ መላው ህዝብ እየተከለ ያለው ችግኝ የቀጣዩን ትውልድ ተስፋን የሚያለመልም የጋራ ሀብት ነው ብለዋል።

ባለፉት ጊዜያት በሀገሪቱ የተተከሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን በማስቀረትና ለምነትን በማሳደግ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም