ኢትዮጵያ የሚለው ስም በጋራ የመቻልና የጽኑ አቋም ተምሳሌት ነው - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሚለው ስም በጋራ የመቻልና የጽኑ አቋም ተምሳሌት ነው - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሚለው ስም በጋራ የመቻልና የጽኑ አቋም ተምሳሌት ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
አገልግሎቱ የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ስንትባበር ምን ማድረግ እንደምንችል ደጋግመን ለዓለም ያሳየንበት የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዛሬም በድል ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ የሚለው ስም በጋራ የመቻልና የጽኑ አቋም ተምሳሌት ነው።
መንግሥት የሀገሪቱን ዘላቂ ጥቅም ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን ሲያስቀምጥ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሀገራዊ ፍላጎቱን በጋራ ተነሣሽነት እውን የማድረግ የዘመናት ልምምድ አለው።
በተለይም መንግሥት ለአረንጓዴ ልማትና ሀገራዊ ከፍታ ለሚያቀርበው ጥሪ ሕዝቡ በላቀ ተሳትፎ ምላሽ የመስጠት ቁርጠኝነቱ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አብነት የሚሆን ነው።
መንግሥት በኢትዮጵያ የተራቆቱ አካባቢዎች በልጆቿ ብርቱ እጆች እንዲታከሙ፣ እየተስፋፋ የመጣው ድርቅና በረሃማነት በዘላቂነት እንዲገታ እና በአስተማማኝ መሠረት ላይ የተገነባ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እውን እንዲሆን ግልጽና ጽኑ አቋም በመያዝ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል።
በዚህም በላቀ የሕዝብ ተሳትፎና በመንግሥት መሪነት ታላቁን የሕዳሴ ግድብ እውን ማድረግ ተችሏል፤ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ላይ ምድራቸውን አረንጓዴ ማልበስ ባህላቸው አድረገውታል ፤ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለው ኢትዮጵያ አረንጓዴ ሸማ ለብሳለች።
ዘንድሮም በንቅናቄው 8ኛው ዓመት በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን፣ በክረምቱ ደግሞ በአጠቃላይ 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል መንግሥት ቁርጠኛ አቋሙን በይፋ አሳውቋል።
ለመንግሥት ሀገራዊ ጥሪ ቀናኢ የሆኑ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችም ይህንን ጥሪ በሙሉ ባለቤትነት ተቀብለው ለስኬቱ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል። በዚህም በዛሬው ዕለት 26 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀምበር ከ805.3 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የተቀመጠውን ግብ ከዕቅድ በላይ አሳክተውታል።
ይህ መንግሥትና ሕዘብ ሲተባበሩ ምን ማድረግ አንደሚችሉ የሚያሳይ፣ ማንም በዓለም ላይ ያለ ሀገር በቀላሉ ሊያሳካው የማይችል ድንቅ ስኬት ነው።
ይህ ውጤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና የመንግሥት ስትራቴጂካዊ አቋም በአንድ አቅጣጫ ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጫ ነው።
በዛሬው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 26 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ብርድ፣ ዝናብና ፀሐይ ሳይበግራቸው መሬት ሲያለምዱ ውለዋል፤ በዚሁ ጽኑ እንቅስቃሴም የዘንድሮው ክረምት ከገባ ጀምሮ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ኮርታለች፤ መንግሥትም የሕዝቡን ከፍተኛ ቁርጠኝነትና ባለቤትነት ባየበት በዚህ ታሪካዊ ክስተት ከፍተኛ ኩራትና ክብር ተሰምቶታል። ይህም መንግሥት ይህንን ታላቅ ሕዝብ በበለጠ ኃላፊነትና ታማኝነት የማገልገል ጽኑ አቋሙን እንዲያጠናክር ተጨማሪ ብርታት ሆኖታል።
ክቡራን ኢትዮያውያን፣ ክቡራን የኢትዮጵያ ወዳጆችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አካላት፤ ዛሬ ይኸንን አገራዊ ራዕይ በጋራ እውን ማድረግ እንድንችል ስላደረጋችሁት ከፍተኛ ርብርብ መንግሥት በኢትዮጵያ ስም ላቅ ያለ ምስጋና ያቀርባል።
የክረምቱን አጠቃላይ የ8 ቢሊዮን ችግኞች ተከላ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ለማሳካት የተጀመረው አገራዊ ተሳትፎና ጽኑ አቋም ተጠናክሮ ይቀጠጥላል።
ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት