የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የድርቅና የጎርፍ አደጋዎችን በመከላከል ውጤት አስገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የድርቅና የጎርፍ አደጋዎችን በመከላከል ውጤት አስገኝቷል
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የድርቅና የጎርፍ አደጋዎችን በመከላከል ውጤት ማስገኘቱን የተለያዩ ክልሎች የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነሮች አመለከቱ ።
የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)ን ጨምሮ የክልል ኮሚሽነሮች፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በሀዋሳ ከተማ በተካሔደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተሳትፈዋል።
የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በየአመቱ ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥ በመዋጋት ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።
እየተካሔደ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ችግር መፍትሔ በመሆን ልምድ የሚወሰድባት ሀገር እንድትሆን እያደረጋት ነው ብለዋል።
ችግኞችን መትከል በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ እንዲሳካ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር አብዱሰላም ሙሴ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት የተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የጎርፍ ስጋት ከመቀነስ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አስችሏል ብለዋል።
በዛሬው እለት የተካሔደው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መላውን ማህበረሰብ ያለ ልዩነት በማሰለፍ መጻኢ ልምላሜና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ነው የጠቀሱት።
የሶማሌ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ የአደጋ ምላሽ ፈንድ ዳይሬክተር አቶ በሽር አረብ ፤ የችግኝ ተከላው በደን ሽፋን መቀነስ ሳቢያ የሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመከላከል መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎች የአፈር ለምነት ከመጨመር ባለፈ ጎርፍና ሌሎች ችግሮችን ለመቀነስ እንዳስቻለም ነው ያነሱት።
በፌዴራል ፖሊስ 6ኛ ሬጂመንት 2ኛ ሻምበል አመራር ዋና ሳጂን አይጎታ አላ በበኩላቸው፤ የሀገርን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ ሁለንተናዊ ልማቷ እንዲጠናከር በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ አሻራ ተሳትፎ መደረጉን ነው የጠቀሱት።