አረንጓዴ ዐሻራ ለመጪው ትውልድ ጽዱና አረንጓዴ የሆነች ኢትዮጵያን የማስረከብ ትውልድ ተሻጋሪ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ ለመጪው ትውልድ ጽዱና አረንጓዴ የሆነች ኢትዮጵያን የማስረከብ ትውልድ ተሻጋሪ ተግባር ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ ለመጪው ትውልድ ሚዛኗን የጠበቀች፣ ለኑሮ ተስማሚ፣ ጽዱና አረንጓዴ የሆነች ኢትዮጵያን የማስረከብ ትውልድ ተሻጋሪ ተግባር መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።
የዘንድሮው "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የ800 ሚሊዮን የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ እየተካሄደ ይገኛል።
የሰላም ሚኒስቴር አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም ተጠሪ ተቋማት በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአዲስ አዳማ ፈጣን መንገድ ዳርቻ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ አረንጓዴ ዐሻራ ሚዛኗ የተጠበቀች፣ ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ የምናወርስበት የታሪካችን አንድ አካል ነው።
መርሃ ግብሩም በአረንጓዴ ኢኮኖሚ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለትውልድ የሚያስተላልፍ የልማት ውርስ መሆኑን አንስተዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራም የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በማሳደግ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ምርታማነት አቅም እየፈጠረ የሚገኝ ውጤታማ የልማት ትልም መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች ሁለንተናዊ ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶና የአርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት በማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ የተተከሉና የሚተከሉ ችግኞችም የአካባቢን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር ለምግብ ዋስትና የሚረዱ የፍራፍሬ እና ለአካባቢ ጥበቃ ጠቀሜታ ያላቸው እንደሆኑም ጠቁመዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞችን ተከታትሎ ማሳደግ፣ መንከባከብና የፅድቀት መጠናቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንገ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም ከምትሰራቸው ስራዎች አረንጓዴ አሻራ ስራ ዋነኛው መሆኑን ገልፀው በዚህም አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።
መርሃ ግብሩ የደን ሽፋን ከመጨመር በላይ የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥ በሚሰራው ስራ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአፈር መሸርሸር፣ ለውሃ ሀብት ጥበቃና ለግብርና ምርታማነት ትርጉም ያለው ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ምክትል ስራ አስፈፃሚ መልእክተ ሳህሉ ናቸው።