ኢትዮጵያውያን ለልጆቻቸው መሰረት መጣል ሲወስኑ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ለዓለም ህዝብ አሳይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ለልጆቻቸው መሰረት መጣል ሲወስኑ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ለዓለም ህዝብ አሳይተዋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያውያን ለነገ ለልጆቻቸው መሰረት መጣል ሲወስኑ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ለዓለም ህዝብ ያሳዩበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ሲካሄድ የዋለው በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ805 ሚሊዬን በላይ ችግኞችን በመትከል ተጠናቅቋል፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ ያሳካችው ድል በብዙ ሀገራት ሊታሰብ ይችላል ነገር ግን በቀላሉ ሊሳካ እንደማይችል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ታላቅ ተግባር የፈጸመው የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቅ ክብር አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም አይነት ክፍያ ሳይከፈላቸው ሙሉ ቀን ያውም በዝናብ ችግኝ ሲተክል መዋል በዋዛ ፈዛዛ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለዚህ ስኬት እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያውያን ምንም ማድረግ እንደሚችሉ በተግባር ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ተደምረን ተስፋን በመትከልና መሰረት በመጣል የነገዋን ኢትዮጵያ የምትበለጽግ፣ የማትለምን፣ ለተቸገሩት የምትደርስ መሆኗን ለአፍሪካም ለዓለምም ማሳየት አለብን ብለዋል፡፡
በመሆኑም በሌሎች ሥራዎቻችን አብሮ በመቆም፣ በመተባበርና በቀና እሳቤ ተስፋን ለልጆቻችን መዝራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ወጥቶ መትከሉ ብቻ ሳይሆን ተቋሞቻችን ያላቸውን ብቃት በተግባር አይተንበታል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያውያን ለነገ ለልጆቻቸው መሰረት መጣል ሲወስኑ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ለዓለም ህዝብ አሳይተዋል ብለዋል፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተስፋን እንተክላለን ብለን ከጀምረንበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 6 ነጥብ 5 ቢሊዬን ችግኝ መትከል ችለናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀሪው 1 ነጥብ 5 ቢሊዬን ችግኝ በቀጣይ ወራት እንደሚተከል ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ከ805 ሚሊዬን በላይ ችግኝ በመትከል ሪከርድ መስበሯንና ማድረግ እንደምትችል ደጋግማ ያሳየችበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡