ቀጥታ፡

ኢዜአ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ህብረተሰቡን ከማንቃት ባለፈ በተግባርም አርአያነቱን እያሳየ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጠናከር የማንቃትና የመቀስቀስ ሚናውን ከመወጣት ባሻገር በተግባርም አርአያነቱን እያሳየ እንደሚገኝ  የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።

"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ተካሄዷል።


 

ኢዜአ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እና ከወረዳ 6 አመራሮች ጋር በመሆን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ አከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በ2018 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለሶስተኛ ጊዜ የችግኝ ተከላ አካሂዷል።


 

ዛሬ በተካሄደው የችግኝ የመትከል መርሃ ግብርም የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች መሳተፋቸውን ተናግረው፤ በቀጣይም የተተከሉትን ችግኞች የመንከባከብ ስራ እንደሚያከናውን ተናግረዋል።


 

ኢዜአ ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ስኬት ህብረተሰቡን የማንቃትና የመቀስቀስ ሚናውን ከመወጣት ባሻገር በተግባርም አርአያነቱን እያሳየ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 6 ዋና ስራ አስፈጻሚ አለማየሁ መርጋ በበኩላቸው፤ የወረዳው ነዋሪ ከለሊት ጀምሮ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በንቃት ሲሳተፍ  መቆየቱን ገልጸዋል።


 

የወረዳው ነዋሪዎች በየጊዜው በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሚያደርጉት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ያነሱት አቶ አለማየሁ፤ በቀጣይም ይህንኑ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።


 

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በከፍተኛ ንቅናቄ ተጀምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በነቂስ ወጥቶ ሲተክል መዋሉን የተናገሩት ደግሞ የክፍለ ከተማው ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ ቅድስት ንጋቱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም