ቀጥታ፡

አረንጓዴ ዐሻራ የተስተካከለ ሥነ-ምኅዳርን በመገንባት የውሃ ሃብት ዘላቂነትን የሚያጎለብት አቅም እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተስተካከለ ሥነ-ምኅዳርን በመፍጠር፣ የውሃ ሀብትን ዘላቂነት በማጠናከርና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን ውጤታማነትን እያጎለበተ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

የዘንድሮው "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የ800 ሚሊዮን የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ተካሄዷል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራርና ሠራተኞች በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳ ወረዳ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ የሚተከሉ ችግኞችም የተፋሰስ ጥበቃን በማጠናከር፣ የውሃ ምንጮችን በማጎልበት፣ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስና የተፈጥሮ ሀብትን ዘላቂነት በማስጠበቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ አንስተዋል።


 

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮች ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው በመሬት ላይ የሚታዩ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥና በሥነ-ምኅዳር ጥበቃ ዙሪያ ከመነጋገር ባለፈ በተግባር እየሠራች ከሚገኙ ሀገራት አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳ ወረዳም የውሃ፣ የኃይል፣ የአካባቢ ጥበቃና የተፋሰስ ልማትን በተቀናጀ መልኩ የሚያከናውን "ስማርት መንደር" ፕሮጀክት እያስፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም የአካባቢ መራቆትና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ የውሃ ምንጮችን በማጎልበት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

የሚተከሉ ችግኞችንም በመንከባከብ ደኅንነቱ የተጠበቀ የውሃ ሀብትና ጤናማ ሥነ-ምኅዳር በመገንባት ለትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ማኅበረሰቡም የተተከሉ ችግኞችን በተገቢው መልኩ እንክብካቤና ክትትል በማድረግ የተፈጥሮ ሀብትን የመጠበቅ ባህል ማዳበር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት ከሀገሪቱ የታዳሽ ኃይል ልማት ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለው ሲሆን፣ በተፋሰሶች ላይ የሚከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የችግኝ ተከላ ሥራዎች የውሃ ምንጮችን በማጎልበት ለሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦች ዘላቂ የውሃ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።

በተለይም የዓባይ ግድብን ጨምሮ የጊቤ፣ የመልካ ዋከና፣ የፊንጫና የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫዎች በብቃት እንዲሠሩ የተፋሰስ ጥበቃና የውሃ ምንጮች ዘላቂነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለኃይል ልማት ስኬትም ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


 

በሚኒስቴሩ የውሃ እና መሬት ሀብት ዋና ዳይሬክተር ጌጤ ዘለቀ (ዶ/ር) ፣የሚተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁና ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ በማድረግ አካባቢውን ወደ ቀድሞ ተፈጥሮአዊ ሁኔታው ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚሁ አግባብ አረንጓዴ አሻራን በማስፋፋት የሀገሪቱን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንዲሁም የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም