ቀጥታ፡

ያቀደችውን በተግባር የምታሳካ ታላቅ ሀገር

የአንድ ሀገር ታላቅነት ከሚለካባቸው ጉዳዮች አንዱ የተያዙ ሀገራዊ እቅዶችን በተግባር የመለወጥ አቅም  ዋነኛው ነው።

ኢትዮጵያም በዛሬው እለት በአንድ ጀምበር ከ805 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ያስመዘገበችው አዲስ ታሪካዊ ስኬት፣ ሀገሪቱ ያቀደችውን በተግባር ማሳየት የምትችልና ትልልቅ ህልሞችን የመተርጎም አቅም ያላት ታላቅ ሀገር መሆኗን ለመላው ዓለም በተግባር ያስመሰከረ  ነው።

ይህ በአንድ ጀምበር የተከናወነ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በርካታ ጥልቅ ትርጉሞችን የያዘ ነው፡

በአንድ ጀንበር ከ805 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ግዙፍ የሎጂስቲክስ፣ የዝግጅትና የህዝብ ንቅናቄ ስራን ይጠይቃል።


 

ይህ ስኬት ሀገሪቱ ማንኛውንም ታላቅ አገራዊ እቅድ አቅዳ እስከ መጨረሻው የትግበራ ምዕራፍ ድረስ በብቃት የመምራትና የማስተባበር ተቋማዊና ህዝባዊ አቅም እንዳላት ማረጋገጫ ነው።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ዕድሜ፣ ጾታ፣ ወይም ልዩነት ሳይለያያቸው በአንድ ቀን ለተመሳሳይ አገራዊ ዓላማ መቆማቸው፣ ኢትዮጵያውያን ለጋራ እድገታቸውና ለሀገራቸው የወደፊት ተስፋ ያላቸውን ጽኑ ፍላጎትና አንድነት አሳይቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥና የበረሃማነት መስፋፋት ዋና ስጋት በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባራዊ እርምጃ ለችግሩ መፍትሔ በመስጠት ረገድ የዓለም አቀፍ መሪነቷን ያስመሰከረችበት አጋጣሚም ጭምር ነው።

ይህ ስኬት ሀገሪቱ የገጠሟትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች ተሻግራ፣ አቅሟን አስተባብራ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምትችል ለዜጎቿም ሆነ ለውጭው ዓለም የሰጠችው ትልቅ የራስ መተማመንና የተስፋ መልእክት ነው።




በአጠቃላይ፣ በአንድ ጀምበር የተከናወነው ይህ ታሪካዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ኢትዮጵያ አርቆ የማሰብና የማቀድ ችሎታዋን ብቻ ሳይሆን፣ ያቀደችውንም በአንድነትና በቁርጠኝነት ወደ መሬት በማውረድ በተግባር የምታሳይ ታላቅ ሀገር መሆኗን በግልጽ ያረጋገጠ አኩሪ ተግባር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም