የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለአካባቢ ጥበቃና ለምግብ ዋስትና የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለአካባቢ ጥበቃና ለምግብ ዋስትና የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ጥበቃን በማጠናከር፣ የአፈርና የውሃ ሀብትን በመጠበቅ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትን በመደገፍ የሀገሪቱን የልማት ጥረት እያጠናከረ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ከበደ ይማም ገለጹ።
"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ነው።
የግብርና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ደን ልማት ተጠሪ ተቋማትም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ በተካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከሰባት አመት በፊት ጀምሮ በሀገራዊ ንቅናቄ እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፣ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ ምርታማነትን በማሻሻልና ለምግብ ዋስትና የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ቀደም ሲል በደን ጭፍጨፋና በአፈር መሸርሸር የተፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ የሀገሪቱን ሥነ-ምህዳር መልሶ ለማገገም ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፤ ይህም የትውልድ ህልውናን ለማስቀጠል የሚደረግ ሀገራዊ ጥረት መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግሥት አመራርና የሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ የፕሮግራሙ ዋነኛ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ የሚታየው ሰፊ ተሳትፎ የአረንጓዴ ዐሻራን ወደ ሀገራዊ ባህል መቀየሩን ያሳያል ብለዋል።
ዘንድሮ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች የአገር በቀል ዝርያዎችን፣ ለምግብና ለፍራፍሬ ምርት የሚውሉ ዛፎችን፣ ለደን ልማትና ለሥነ-ምህዳር ጥበቃ የሚያገለግሉ ዝርያዎችን እንዲሁም ለከተማ አረንጓዴ ልማት የሚውሉ ችግኞችን ያካተቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተራሮቿ ላይ የምታከናውነው የደን ልማት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ዘላቂ ፍሰት እንዲኖራቸው በማድረግ ለጎረቤት ሀገራትና ለቀጠናው ሥነ-ምህዳር መረጋጋት ከፍተኛ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የግብርና ሚኒስቴር ሴቶችና ማህበራዊ አካቶ ተግባራት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ገነት አብደላ በበኩላቸው፤ የችግኝ ተከላ ለነገ ትውልድ የሚተላለፍ ጠቃሚ ሀብት መሆኑን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ የአፈር መሸርሸርንና የጎርፍ አደጋን በመቀነስ፣ አካባቢን በመጠበቅ፣ ለምግብ ሉዓላዊነት መሳካትና ለዘላቂ የግብርና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያም በዚህ ዘርፍ ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል።