የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እያነጸ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እያነጸ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በጽኑ መሠረት ላይ እያነጸ እንደሚገኝ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ሀገራዊ ግብ ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በይፋ እየተካሄደ ይገኛል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አመራሮች እና ሠራተኞች “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሐሳብ በቢሾፍቱ ፈጣን መንገድ ላይ ችግኞችን ተክለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ መርሃ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና በሀገሪቱ የተዘረጋውን የአረንጓዴ ትራንስፖርት ስትራቴጂ ለማገዝ ከፍተኛ ሚና አለው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል፣ የውሃ ሀብትን ለመጠበቅ እና ለተተኪው ትውልድ የሚተርፍ የተፈጥሮ ፀጋን ለማስረከብ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተተከሉ ችግኞች የደን ሽፋን ከመጨመር ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረጉ ሥራዎች ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ አውስተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በከተሞች አካባቢ ደንን ማስፋፋት የከተሞችን ሙቀት በመቀነስ ሰዎች በእግር ወይም በብስክሌት በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የምታደርገውን ሽግግር በዋናነት የምትደግፈው በኤሌክትሪክ ኃይል በመሆኑ፣ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የዝናብ ዑደትንና የግድቦችን ደህንነት በመጠበቅ አስተማማኝ ንጹህ ኃይል እንዲኖር እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
መርሃ-ግብሩ ሀገሪቱ የያዘችውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በጽኑ መሠረት ላይ የሚጥል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍራኦል ጣፋ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።
ባለሥልጣኑ ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የተሻለ የጽድቀት ምጣኔ እንዲኖር ሲሰራ መቆየቱንና ይህንን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዮሐንስ አበራ በበኩላቸው ዓለም በካርበን ልቀት ምክንያት እየተፈተነች እንደምትገኝ ገልፀው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ይህንን ለመከላከል አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት ዋና ዳይሬክተር አስካለ ተክሌ በበኩላቸው፤ በትራንስፖርት ዘርፉ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመከላከል በመርሃ ግብሩ ተሳታፊ በመሆን ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተከታትሎ የመንከባከብ ስራም እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል።