ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለነገ ትውልድ የሚተርፍ የብልፅግና ጉዞ መሰረት ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ ያለው እና ለነገ ትውልድ የሚተርፍ የብልፅግና ጉዞ መሰረት ነው ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ።

"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው።


 

የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር በአዲስ አዳማ ፍጥነት መንገድ ላይ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አካሂደዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ቡና፣ ፍራፍሬና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ናቸው የተተከሉት።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን ከመሸፈን ባለፈ ለነገ ትውልድ የሚተርፈው የብልፅግና ጉዞ መሰረት ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር አረንጓዴ የለበሰች ከተፈጥሮ ጋር የተስማማች ሀገር መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።


 

ባለፉት ዓመታት የተተከሉት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል።

 

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር የኢትዮጵያውያን አቅም የተገለፀበት የመቻልና የማድረግ ማሳያ ነው ብለዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር የሚተከሉ ችግኞች ሀብት መፍጠር የሚያስችሉ እየሆኑ መምጣታቸውን አንስተው ችግኝ የመትከል ተግባር ማህበራዊ ባህል እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት።

በዛሬው የአንድ ጀምበር መርሃግብር የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሰራተኞች ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በትጋት ችግኝ እየተከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ነጋችንን ዛሬ የምንሰራበት ባህል በመሆኑ ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርና የችግኝ ተከላ መርሃግብሩ አስተባባሪ ደስታው መኳንንት(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዛሬው እለት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መልከ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተተክለዋል።


 

የችግኝ ተከላ መርሃግብር ስነምህዳርንና የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ የሚያስችል በመሆኑ ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ የለበሰች ሀገር ለማሻገር ህብረተሰቡ መረባረብ እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ(ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር እንደሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ አህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተዋፅኦ ያለወ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ስለሆነም ችግኝን ከመትከል ባለፈ በመንከባከብ እንዲፀድቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር የውሃ አካላትን መልሰው እንዲያገግሙና የአፈር ለምነትን ለመመለስ የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ቦንሳ ባይሳ ናቸው። 


 

ህብረተሰቡ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በመገንዘብ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም