ቀጥታ፡

አረንጓዴ ዐሻራ ፅዱና ማራኪ ከተሞችን በመፍጠር ለነዋሪዎች ምቹ የከተሜነት ምህዳር እየገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ፅዱና ማራኪ ከተሞችን በመፍጠር ለነዋሪዎች ምቹ የከተሜነት ምህዳር እየገነባ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡

"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ሀገራዊ መርሃ ግብር ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ እየተካሄደ ይገኛል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትም በዚሁ ሀገራዊ መርሃ ግብር በመሳተፍ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ወቅት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአብሮነትን መንፈስ በማጠናከር፣ ሀገረ መንግሥትን በመገንባትና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።


 

መንግሥት የሕዝብን ተሳትፎ በማሳደግ የሚተከሉ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በአግባቡ በመንከባከብ እስከ ፍሬ እንዲደርሱ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምም የከተማ ግብርናን በማስፋፋት፣ የአካባቢ ጥበቃና ውበትን በማጎልበት፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና የኑሮ ደረጃቸውን በማሻሻል ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከተሞች የመኖሪያ ስፍራ ብቻ ሳይሆኑ የምርት ማዕከላት እንዲሆኑ ታስቦ የተነደፈው ፕሮግራም የተተከሉ ችግኞችን ከመንከባከብ ጀምሮ ለምርት እስኪደርሱ ድረስ ክትትል የሚደረግበት መሆኑንም አብራርተዋል።

አረንጓዴ ልማቶች የዜጎችን ተጨማሪ ገቢ ከማሳደግ ባለፈ፣ ከተሞችን ምቹ፣ ንጹሕና አረንጓዴ በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ ተስማሚ የኑሮ አካባቢ ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም