የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እይታ - ኢዜአ አማርኛ
የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እይታ
ዛሬው በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ሀገራዊ መርሃ-ግብር በመላው ኢትዮጵያ እየተካሄደ ይገኛል።
ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በነቂስ በመውጣት በዚሁ የታሪክ አካል በሆነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በንቃት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት አረንጓዴ ዐአሻራቸውን አኑረዋል።
በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልእክት ዛፍ ተስፋ ነው፤ እየተከልን ያለነው ነገን እና የልጆቻችንን መጻኢ ዕድል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በጀመሩት አንድነትና መተባበር የያዙትን ሀገራዊ ዓላማ ከግብ እንዲያደርሱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሯ ስር በአንድ ቀን ውስጥ 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ያቀደችው ይህ ሀገራዊ ግብ የበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረትም ስቧል።
የቻይናው ሲጂቲኤን ባወጣው ዘገባ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ መላው ኢትዮጵያዊ ሀገራዊ ምላሽ በመስጠት በችግኝ ተከላው ላይ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጿል።
ይህ ዘገባ አክሎም፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ የ800 ሚሊዮን ችግኞችን የአንድ ጀምበር ተከላ መርሃ-ግብር በስኬት እያካሄደች መሆኑንም አመልክቷል።
የኳታሩ አልጄዚራ በበኩሉ፣ ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2027 የምታስተናግደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ዝግጅት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጠናክር እና የሚደግፍ መሆኑን አብራርቷል።
የኮሪያ ሪፐብሊኩ ዘ ኮሪያ ፖስት ያጋራው መልዕክት ደግሞ ይህ ታሪካዊ ዘመቻ የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሽግግር የሚያፋጥን ትልቅ የለውጥ ምሰሶ መሆኑን በዘገባው አጉልቶ አሳይቷል።
ጋዜጣው "ተስፋን መትከል፡ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እና የሀገራዊ ለውጥ ኃይል" በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሁፍ ይህንኑ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ዳስሷል።
የሶማሊያው ሆርን ዲፕሎማት በበኩሉ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የያዘችው እቅድ የደን መጨፍጨፍን ለመግታት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም እና የህዝቡን ንቁ ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ገልጿል።
የኩባው ፕሬንሳ ላቲና በበኩሉ፣ ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ውስጥ ያንን ያህል ቁጥር ያለው ችግኝ በመትከል ሌላ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ እና ስኬት እያስመዘገበች መሆኑን ዘግቧል።
ይህ የችግኝ ተከላ ከሀገር ውስጥ አልፎ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ አጉልቶ ያሳየ መሆኑን የፓኪስታኑ ኦሶሲዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።
በፓኪስታን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሀገሪቱን ግብ ለመደገፍ እና በሀገራቱ መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር ያለመ የችግኝ ተከላ ማካሄዱንም ጠቁሟል።
የዩጋንዳው ቻርማር እንዳመለከተው፣ ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ውስጥ 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብ በማስቀመጥ የጀመረችው ይህ ዓመታዊ ንቅናቄ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዘላቂ ልማት እና ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ማሳያና አርዓያ መሆኑን ገልጿል።