ቀጥታ፡

በካፋ ዞን የሻይ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በይፋ ተጀመረ

ካፋ፤ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በካፋ ዞን የሻይ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀመረ።

የሻይ ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በካፋ ዞን ሺሾ እንዴ ወረዳ ዋና ቦላ ቀበሌ በዛሬው እለት ተከናውኗል። 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፤ የሻይ ልማትን ለማስፋት የተያዘውን እቅድ መሰረት በማድረግ በዞኑ አራት ወረዳዎች ችግኝ የማዘጋጀት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም በአራት የችግኝ ጣቢያዎች 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሻይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አንስተው የመትከል ስራው በዛሬው እለት በይፋ መጀመሩን ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረትም ከዛሬ ጀምሮ በቀጣዮቹ ተከታታይ 15 ቀናት  በተዘጋጀው 110 ሄክታር መሬት ላይ የመትከል ስራው የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።

የሺሾ-እንዴ ወረዳ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ስራ ልማት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አዱኛ አለሙ፤ በበኩላቸው በወረዳው የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬና የውጭ ምንዛሬን ለማያስገኙ ለቡናና ሻይ ችግኞች ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል። 


 

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ ጋር በማያያዝ የሻይ ችግኞችን በማዘጋጀት በዛሬው እለት በዋና ቦላ ቀበሌ ተከላ መጀመሩን ገልጸዋል።

በወረዳው 43 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ለሻይ ልማት መዘጋጀቱን ጠቅሰው የችግኝ ተከላው ይቀጥላል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ለይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ካሳሁን ታዬ፤ በክልሉ በዘንድሮው ዓመት ለሻይ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት የተሟላ ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በተያዘው እቅድ መሰረትም ዘንድሮ የሻይ ችግኝ ተከላ በብዛት የሚከናወን ይሆናል ብለዋል።


 

ከዋና ቦላ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ጌታቸው ወልደጊዮርጊስ እና አቶ ንጉሴ ገብረሚካኤል የልማት ስራው በብዙ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም