ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተሻለች ሀገርን ለእኛ ለማስረከብ የሚደረግ ጥረት በመሆኑ በመሳተፋችን ደስተኞች ነን -ታዳጊዎች

አሶሳ፤ ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተሻለች ሀገርን ለእኛ ለማስረከብ የሚደረግ ጥረት በመሆኑ በመርሃ ግብሩ በመሳተፋችን ደስተኞች ነን ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተሳተፉ ታዳጊ ወጣቶች ተናገሩ።

ከታዳጊዎች እስከ አዋቂዎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ዞን አቡራሞ ወረዳ እየተካሄደ በሚገኘው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተገኙ ታዳጊዎች፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለታዳጊዎች የተሻለች ሀገር ለማስረከብ የሚያግዝ ትልቅ ስጦታ መሆኑን ገልጸዋል።

ታዳጊዎቹ አክለውም፤ ''የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተሻለች ሀገርን ለእኛ ለማስረከብ የሚደረግ ጥረት በመሆኑ በመሳተፋችን ደስተኞች ነን'' ብለዋል።

ታዳጊ ወጣት ሳላዲን ሙሳ፤ ችግኝ መትከል የተስተካከለ ተስማሚ አየር እንዲኖርና ምንጭ እንዲፈልቅ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግሯል።

በትምህርት ቤትም ስለ አካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ እየተማሩ መሆኑን ገልጾ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ በመሳተፉ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

ሌላው ታዳጊ አህመድ አሊ፤ ወላጆቹ በየዓመቱ የሚተክሏቸው ችግኞች ጥቅም መስጠት መጀመራቸውን በመግለጽ፣ ችግኞችን መትከል ሀብትን ለትውልድ ማስተላለፍ በመሆኑ እኛ ታዳጊዎች የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን ብሏል።

በየዓመቱ በሚከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከአባቱ ጋር በመሆን እየተሳተፈ መሆኑን የገለጸው ሌላው ታዳጊ ፋህሚ ሙፍቲ፤ ኅብረተሰቡ በችግኝ ተከላው እያደረገ ያለው ከፍተኛ ተሳትፎ አግራሞት እንደፈጠረበትና እንዳስደሰተው ተናግሯል።

አክሎም ታዳጊዎች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሳተፋቸው የችግኝን አስፈላጊነት እንዲረዱ እና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ይዘው እንዲያድጉ እንደሚያግዛቸውም አብራርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም