ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊቱ  ሀገራዊ ግዳጁን  ከመወጣት ባሻገር  የልማት ስራዎች ላይ መሳተፉን ይቀጥላል

ሐረር፤ሐምሌ 27/2018 (ኢዜአ)፦ መከላከያ ሰራዊቱ  ሀገራዊ ግዳጁን  ከመወጣት ባሻገር  የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ  የህዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያረጋገጠ ይቀጥላል ሲሉ የምስራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ፍቃዱ ጸጋዬ ተናገሩ።

የሰራዊቱ አባላት ከሐረሪ ክልል ማህበረሰብ ጋር  በመሆን የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አከናውነዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የምስራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ፍቃዱ ጸጋዬ እንዳሉት፤ሰራዊቱ የሀገርን ሉአላዊነት  ከማስጠበቅ ባሻገር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።

 ባለፉት ሰባት ዓመታትም የአረንጓዴ አሻራውን ከማኖር ባሻገር ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ስራዎች ጋር  በቅንጅት  እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሰራዊቱ በግብርናው ዘርፍም ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ በመሳተፍ  የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ በማድረግ ስራ ላይ የሕዝብ ወገንተኝነቱን እያሳየ  እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በየአመቱም በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር እየተሳተፉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የምስራቅ እዝ አባል  ኮሎኔል ስሜነህ ብርሃኑ ናቸው።


 

የሰራዊቱ አባላትም  ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ እንዲጸድቁ በማድረግ  እየሰሩና የምርቱም ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።


 

ሻለቃ ሃይሉ ታሪኩ በበኩላቸው፤ ሰራዊቱ  ከተሰጠው ግዳጅ ጎን ለጎን የችግኝ ተከላና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ላይ  በትኩረት እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም